Fana: At a Speed of Life!

ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ66 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2012 በጀት ዓመት ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ66 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2012 በጀት ዓመት 56 ነጥብ 92 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ከ66 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለም ነው ባወጣው መረጃ ያመለከተው።

ይህም የዕቅዱን 116 ነጥብ 5 በመቶ በማከናወን ከዕቅድ በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጿል።

በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው ገቢ 37 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከጅቡቲ የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 29 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ደግሞ ከሱዳን የተገኘ ነው ተብሏል።

በዚህ ዓመት ከሁለቱ ሀገራት የተገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ገቢ ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ እንዳለው ተነግሯል።

የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውኃ መያዛቸውና የኃይል መቆራረጥ መቀነሱ ለዕቅዱ መሳካት አስተዋጾ ማድረጉ ተብራርቷል።

በቅርቡም ለኬኒያ የኤሌክቲክ ኃይል በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እና የኤሌክትሪክ ኮንቨርተር ጣቢያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያስታወቀው

ኢትዮጵያ ከሶስቱ ሀጋራት በተጨማሪ በቀጣይ ከሶማሌ ላንድ፣ ከታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ እንደምትገኝም አስታውቋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.