Fana: At a Speed of Life!

ለጎብኚዎች ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጎብኚዎች ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ተመረቁ፡፡

ኦክሎክ ጀኔራል ትሬዲንግ የሚገጣጥማቸውና በሄሎ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የጎብኚዎች አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በተገኙበት በይፋ ተመርቀዋል፡፡

የኦክሎክ ጀኔራል ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ሶሎሞን ሙሉጌታ ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላት በመሆኗ ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ቀድመን ለማዘጋጀት ችለናል ብለዋል፡፡

የሄሎ ታክሲ መስራችና ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በበኩላቸው ሄሎ ታክሲ በቀጣይም ጎብኚዎችን በአውሮፕላን ወደ መዳረሻዎች ለማድረስና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት 50 በመቶ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ኦክሎክ ጀኔራል ትሬዲንግም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ110 ስራ አጥ ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ብድር የሚሰጡ ሄሎ ታክሲዎችን፣ 10 የጎብኚ አምቡላንሶችን እንዲሁም በ59 ቋንቋዎች የማስተርጎም ስራ የሚሰሩ 50 ማሽኖችን ለዶክተር ሂሩት ካሳው አስረክበዋል፡፡

የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ ለ250 ሰዎች አሮጌ ታክሲያቸውን ብቻ ሰጥተው አዲስ ታክሲ እንዲረከቡ የሚያስችል ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን የታክሲ ማኅበራትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምስጋና ስጦታ አበርክተዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር ዶክተር ሂሩት ካሳው መንግስት የታክሲ ሞተሮች ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ የወሰነው አሮጌ መኪኖችን በአዲስ በመተካት የአየር ብክለት እንዲቀንስ፣ ሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙ ተጨማሪ የስራ እድል ስለሚፈጥሩ እና ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲከብሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለታክሲ ሾፌሮችም የክህሎትና የአገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል ማለታቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንዲሳተፉ የችግኝ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን ከሄሎ ታክሲ ድርጅት ጋርም በጎብኚዎች የታክሲ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.