Fana: At a Speed of Life!

ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ደስተኛ ህይዎት ለመኖር እንደሚያግዝ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ለዚህ ደግሞ ከአመጋገብ ስርዓት ጀምሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነው፤ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ባለሙያዎቹ ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ይረዳሉ ያሏቸው ምክረ ሃሳቦች ናቸው።

1. የተለያዩ አይነት ምግቦችን መመገብ

ሰውነት ከ40 በላይ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ይፈልጋል ይህን ደግሞ አንድ ሳይሆን የተለያዩ አይነት ምግቦችን በመመገብ ማግኘት ይቻላል።

ምሳ ላይ የቅባት መጠናቸው ከፍ ያለ ምግብ ከተመገቡ በእራት ሰዓት ተቃራኒውን ማድረግ፤ አልያም ዛሬ ስጋ ከተመገቡ ነገ አሳ መመገብ።

2. በካርቦ ሃይድሬት የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ

ለሰውነት ከሚያስፈልገው ንጥረ ነገር ግማሹ በካርቦ ሃይድሬት ከበለፀጉ ምግቦች ነው የሚገኘው።

እንደ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ድንች እና ዳቦ ከመሳሰሉት ይህን ማግኘት ይቻላል።

በቀን በሚመገቧቸው ምግቦች ውስጥ ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ማካተት ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

3. የቅባት መጠናቸው ከፍ ያሉ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስ

የቅባት መጠናቸው ከፍ ያሉ ምግቦች ለሰውነት አስፈላጊ ቢሆኑም፥ መጠናቸው ሲበዛ ግን ለጤና አደገኛ ናቸው።

ከዚህ አንጻርም በሚመገቡት ስጋ የስብ ክምችት ያለበትን በማስወገድ እንዲሁም የአትክልት ዘይቶችን መጠቀም ይመከራል።

4. አትክልትና ፍራፍሬዎችን በብዛት መመገብ

አትክልትና ፍራፍሬዎች ሲመገቡ በቂ ቪታሚን፣ ማዕድን እና አሰር (ፋይበርን) ያገኛሉ።

ከዚህ አንጻር በቀን ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ፤ ቁርስ ላይ አንድ ብርጭቆ የፍራፍሬ ጭማቂ እና በእያንዳንዱ ምግብ ላይ የተለያዩ አትክልቶች ቢኖሩ መልካም ነው፡፡

5. ጨው እና ስኳር መቀነስ

ከፍተኛ የጨው መጠን መውሰድ የደም ግፊትን በማስከተል የልብና የደም ቧንቧን የማጥበብ እድሉ ከፍተኛ ነው።

ስለሆነም ምግብ በሚበስልበት ጊዜ ጨውን በቅመሞች መተካት፤ የስኳር ምግቦች እና መጠጦች ደግሞ በፍራፍሬ በመተካት ጤንነትን መጠበቅ።

6. መደበኛ የምግብ ሰዓትን ጠብቆ መመገብ

የምግብን ሰዓትን ማሳለፍ ለድካምና ረሀብ ያጋልጣል ይህም ሰውነት አቅም እንዲያጣ ያደርገዋል።

መደበኛ የመመገቢያ ሰዓትን ጠብቆ መመገብና በተገቢው መጠን የተለያዩ የምግብ አይነቶች መመገብ አስፈላጊ ነው፡፡

7. በቀን ብዙ ፈሳሽ መጠጣት

አዋቂዎች በቀን ቢያንስ 1 ነጥብ 5 ሊትር ፈሳሽ መጠጣት አለባቸው፤ ውሃ፣ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ ሻይ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ወተትና ሌሎች መጠጦች መውሰድ ተገቢ ነው።

8. የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር

ከመጠን በላይ ውፍረት የስኳር በሽታ፣ የልብ በሽታ እና ካንሰርን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች የመያዝ እድልን ይጨምራል።

አመጋገብን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር ተገቢ ነው።

9. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ካሎሪዎችን ለማቃጠል፣ ለተስተካከለ የልብ እና የደም ዝውውር ስርዓት፣ የሰውነትን ጡንቻ ለማጠንከርና አጠቃላይ ጤናን ለማሻሻል ይረዳል።
ከዚህ አንጻርም በሳምንት ለ150 ደቂቃዎች መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ምንጭ፡- www.eufic.org/en

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.