Fana: At a Speed of Life!

ለጤና ሚኒስቴር 8 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የኮሮና ቫይረስ መከላከያና መመርመሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጤና ሚኒስቴር ከአራት ደርጅቶች 8 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የኮሮና ቫይረስ መከላከያና መመርመሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መረከቡን አስታወቀ፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡

ድጋፍ ካደረጉት መካከል በጀርመን ፍራንክፈርት የሀመረ ብርሀን ቅዱስ ገብርኤል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዩን ብር በላይ የሚያወጣ ዘመናዊ የፒሲአር መመርመሪያ ማሽን አበርክተዋል፡፡

የአራ ዳሎል ኩባንያ በአፋር ክልል ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ ለህክምና ባለሙያዎች የሚያገለግል 124 ሺህ 800 ኤን 95 ማስክ አስረክበዋል፡፡

የየኔታ ቤት የህፃናት ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ በኢትዮጵያ ልጆች ስም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኤን 95ና ሰርጅካል ማስክ ለግሰዋል፡፡

እንዲሁም ፒውር ውድ ፓል ፔፐርና ፓኬጅንግ ፒኤልሲ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰርጅካል ማስኮችን፣ 9 ሙቀት መለኪያዎችንና የጤና ባለሙያዎች አልባሳትን አበርክተዋል፡፡

የጀርመን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናንን በመወከል ድጋፋን ያስረከቡት የምስራቅ ወለጋ፣ የምስራቅ ሸዋና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቤተክርስቲያን ባለባት ነብስና ስጋን የመጠበቅ ኃላፊነት ምዕመናን ከፀሎት ባሻገር ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን መከተል ይገባቸዋል ሲሉ አንስተዋል፡፡

የአራ ዳሎል ተወካይ ከዚህ በፊት በአፋር ክልል ድጋፍ እንዳደረጉ አስታውሰው አሁንም ካደረጉት ድጋፍ አንድ አምስተኛውን ለአፋር ክልል እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የየኔታ ቤት ተወካይ ለልጆች ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት በሚከፈትበት ወቅት ምንም እንኳ ከጓደኞቻቸው ጋር መነፋፈቅ ቢኖርም እንኳ አስተማሪዎቻቸው በሚነግሯቸው መሰረት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡

የፒውር ውድ ፓል ፔፐርና ፓኬጅንግ ፒኤል ሲ ተወካይም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየተወጡ መሆኑንና ይህ ድጋፍም አንዱ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፍ ሰጭዎችን የአሁኑን ጨምሮ እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ወደፊትም ድጋፉ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.