Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ በልዩ ድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡

በዓሉ ”ኢትዮጵያ እንደገና ጥምቀትን በጎንደር“ በሚል መሪ ሀሳብ አብሮነትን በሚያጠናክርና ቱሪዝምና ኢንቨስትመትን በሚያነቃቃ መልኩ ይከበራል ተብሏል፡፡

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ እንደገለጹት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ጎንደር ለኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ አብሮነትና ክብር ከትናንት እስከዛሬ እየተጫወተች ያለውን ሚና በሚዘክርና አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ ይከበራል፡፡

በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገር የአስመራ ከተማን አስተዳደርና ህዝብ ለበዓሉ ጋብዟል፡፡

ማኀበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ ባለው በዓል የቀደመ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦችን ጠንካራ የታሪክና የባህል ግንኙነት በማሰብ የአስመራ ህዝብ ለበዓሉ ጎንደር እንዲገኝ የመጀመሪያው ጥሪ መተላለፉን በመምሪያው የባህል ዕሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና ገብረመስቀል ተናግረዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በጎንደር ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ መልኩን በጠበቀ አግባብ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን በመጥቀስም፥ ከበዓሉ ቀደም ብለው ባሉት ቀናት የአካባቢውን ባህል፣ ወግና ታሪክ ለማስተዋወቅ አላማ ያደረጉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይም የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 202ኛ ዓመት የልደት በዓል የከተማዋ አመራሮች፣ የታሪክ ምሁራንና ነዋሪዎች በተገኙበት በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ታስቧል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናትም የባህል ኤግዚቪሽን፣ የጎዳና ላይ የኪነ ጥበብ ትርኢት እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡

በባህል ሳምንቱ የሚከናወኑ ዝግጅቶች የጎንደርና አካባቢውን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ያለሙ ናቸው፡፡

በተያያዘም በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ሃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ አረጋግጠዋል፡፡

የከተማው ፖሊስ ከህብረተሰቡ በተለይ ከወጣቱ ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ የጸጥታ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ አቀባበል ስርአት እንደሚያስተናግዱ ገልጸው ሁሉንም ለጥምቀት በዓል ጋብዘዋል፡፡

አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችም ለጥምቀት በዓል ለእንግዶች መልካም መስተንግዶ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በነብዩ ዮሐንስ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.