Fana: At a Speed of Life!

ለፍትሕ ስርዓቱ ግልጽነት የሚፈጥሩና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችና አዋጆች ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው-ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፍትሕ ስርዓቱ ግልጽነት የሚፈጥሩና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሕጎችና አዋጆች ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለፀ።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መሆኑ ይስተዋላል።

ለማንኛውም ሕዝብ በሕግ እውቅና ካገኙ መሰረታዊ መብቶች መካከል ፍትህ ማግኘት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል።

በኢትዮጵያም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 37 ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ ውሳኔ /ፍርድ/ የማግኘት መብት እንዳለው ያረጋግጣል።

ለዚህም በተለይ የፍትህ ተደራሽነትን ለማሻሻል የፍትህ አሰጣጥ መንገዶች ከተገልጋዮች ፍላጎት ጋር እንዲጣጣሙ የማድረግ አስፈላጊነት ይገለጻል።

ለዚህም በአገሪቷ የፍትህ ስርዓት ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመፍጠር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሕጎችና አዋጆችን የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለኢዜአ እንደገለጹት በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሕዝብ አመኔታም እንዲኖር የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ መዋቅራዊና ሕጋዊ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የጸረ ሽብር እና የበጎ አድራጎት አዋጆች እንዲሁም ከምርጫ ጋር የተያያዙ አዋጆችን ከተሻሻሉት መካከል ጠቅሰዋል።

የፍርድ ቤቶች፣ የዳኞች አስተዳደር፣ የማረሚያ ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጆችም ከተሻሻሉት አዋጆች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አክለዋል።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የፍትህ አሰጣጥ አገልግሎቱን በማጠናከር የሕግ የበላይነትን በጠንካራ ሁኔታ የማስከበር ስራው የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብትም በማይካድራ፣ በመተከል፣ በጉራፈርዳና በሌሎችም የተከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶችን ለማስቆም፣ ፍትህ ለማስፈንና የሕግ የበላይነት ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ከፍርድ ቤቶች ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በ1998 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ፖሊሲ እንዲሻሻል የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ገልጸዋል።

ይህ የወልጀል ፖሊሲ አገሪቷ አሁን ካለችበት ለውጥ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የሕግ የበላይነትን በተገቢው መንገድ ማስከበር በሚያስችል መልኩ እንዲተገበር ለማድረግ ፖሊሲውን እንደገና የማሻሻል ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የሚሻሻለው የወንጀል ፖሊሲ ተጠናቆ መተግበር ሲጀምር በተለይ በሴቶች  ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና የተደራጁ ወንጀሎችን በመከላከል የሕግ የበላይነት ለማስከበር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

ፖሊሲውን ተከትለው ለሚወጡ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አዋጆች መነሻ ሆኖ ወጥ የሆነ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ ረገድም እገዛ ያደርጋል ብለዋል ።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.