Fana: At a Speed of Life!

ለ14 ዓመታት ግንባታው የተጓተተው የቦረና ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት ባለመስጠቱ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ14 ዓመታት ግንባታው የተጓተተው የቦረና ውሃ ኔትወርክ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ለችግር መዳረጋቸውን የቦረና ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ስምንት ወረዳዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና የዞኑን አርብቶ አደሮች ህይወት ያሻሽላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በ2000 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ቢያዝለትም ዛሬም ወደ ስራ አልገባም ተብሏል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ይደረግባቸዋል በተባሉ ወረዳዎች ላይ ባደረገው ቅኝት የውሃ መሳቢያ ጀኔሬተሮች ያለጥቅም ወድቀው፣ ረጃጅም ጉድጓዶች ያለጥቅም ተቆፍረው፣ የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን ተመልክቷል፡፡

የዞኑ አርብቶ አደሮችም ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ባለመግባቱ በተደጋጋሚ በድርቅ እየተጎዱ መሆናቸውን ገልጸው÷ የቦረና ውሃ ኔትወርክ ተሰርቶ ጥቅም ላይ ቢውል ከብቶቻችንን አናጣም፣ በድርቅ ምክንያት ለስደት አንዳረግም ነበር ብለዋል፡፡

ገልቻ ሳሪቴና መጋዶ ፎሮሌ የተባሉት ሁለት ምዕራፎችም ቢሆኑ ገና በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አቦማ ተሬሳ እና የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዋቆ ሊበን ችግሩ የተፈጠረው በዲዛይን ችግርና በፋይናንስ እጥረት እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው÷ ከሰፊው ስራ ጥቂቱ እንኳን በአግባቡ አለመከወኑን ተናግረዋል፡፡

ከ5ቱ ምዕራፎች ሁለቱን እስከ ሰኔ 30 ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸው÷ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ሌሎቹን ምዕራፎች ለማስፈፀም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ኃላፊው÷ ጥናት መጠናቱን እና ገንዘቡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እንደተገኘ እንዲሁም በቀጣዩ አመት ስራው እንደሚጀመር አመላክተዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.