Fana: At a Speed of Life!

ለ315 ኢንተርፕራይዞች እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ታዳጊ መካከለኛ ባለሃብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር ተካሄደ።

በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ እና የፌዴራል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ዕውቅና የተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች ለመካካለኛ ኢንዱስትሪ የተቀመጠውን ሃብት ያፈሩ፣ ተተኪ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋትና በጥራት ማምረት የቻሉ፣ የገበያ አድማሳቸውን ያሰፉ እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የጀመሩ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት መስፈርቶቹን ያሟሉ እና በስራቸው ስኬታማ የሆኑ 315 ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረዋል።

በ7ኛው ዙር ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩት እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ከምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የዕውቅና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል።

ዕውቅናው በቀጣይ በዘርፉ የተገኙ ተሞክሮዎችን ለማስፋትና ለዘርፉ የተቀረጹ ፖሊሲዎች ተጨባጭ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ነው የተገለጸው።

ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ ከሚያደርግባቸው ስራዎች መካከል የኢንተርፕራይዞች ስራ በዋነኛነት የሚጠቀስ መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመዲናዋ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.