Fana: At a Speed of Life!

ሐምዛ አብዲ ባሬ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐምዛ አብዲ ባሬ አዲሱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ተገለጸ፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ ማህሙድ÷ ሐምዛ አብዲ ባሬን የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው ተዘግቧል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ፥ በቀጣዮቹ ቀናት ካቢኔያቸውን በማዋቀር አገራቸው ያለባትን መሰረታዊ ችግሮች ለማቃለል ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የ48 ዓመቱ አዲሱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ፥ የከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ካለው የጁባ ግዛት የንግድ ማዕከል ከሆነችው ከኪስማዮ ከተማ በሕዝብ ተመርጠው ነው የአገሪቱ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ለመሆን የቻሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ ባሬ፥ በቅርቡ ሶማሊያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለ22 ወራት ያገለገሉትን ሞሀመድ ሁሴን ሮብሌን ነው የሚተኩት።

አዲሱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሹመታቸው በኋላ ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ ማህሙድ ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫ ፥ “ይህን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጣ እምነት ስለተጣለብኝ፣ ሥራዬን የተሳካ ለማድረግ ቀንም ሌትም እሰራለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል።

ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ ማህሙድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ለማካሄድ የታሰበውን የሪፎርም አጀንዳ በመፈጸም ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ባሬ፥ በተለያዩ የመንግስትና የፖለቲካ የኃላፊነት ቦታዎች የሰሩ ሲሆን፥ በተለይም በፈረንጆቹ ከ2011 እስከ 2017 የሰላምና የልማት ፓርቲ (PDP) ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል።

እንዲሁም አሁን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ የሚመሩትና በአገሪቱ ከፍተኛ ደጋፊ አላቸው ከሚባሉት ጠንካራ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ህብረት ለሰላምና ልማት (UDP) ፓርቲን በመመስረት ሂደት ቁልፍ ሰው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ምንጭ ፦ ሲ ጂቲ ኤን እና ኤ ኤፍ ፒ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.