Fana: At a Speed of Life!

ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሕገ-መንግስታዊ መሰረት አለ – የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ሕገ-መንግስታዊ መሰረት እንዳለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-መንግስታዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን ማራዘሙን ጠቅሰው፥ ሆኖም ለሕገ-መንግስቱ ተገዥ ያልሆኑና ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ሕዝቡን የማወናበድ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የትግራይ ክልል መንግስት መሆኑን የገለጹት አቶ አደም ፋራህ “በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ክልሉ ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።

ምርጫ ማስፈጸም የምርጫ ቦርድ ስራ ሆኖ ሳለ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መልኩ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም፤ አግላይ በሆነ መንገድ ምርጫ ማካሄዱን አንስተዋል።

ክልሉ ይህን ድርጊት ፈጽሞ በመገኘቱ ሕገ-መንግስታዊ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል በቂ የሕገ-መንግስት መሰረት እንዳለ አመልክተዋል።

ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ሕግ አውጭውንና ሕግ አስፈጻሚውን ማገድ የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ አካሄድ አንዱ መሆኑን ነው አፈጉባዔው የገለጹት።

ይህንን ተከትሎም ለፌደራል መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግስት ማቋቋምና የፌደራል የፀጥታ አካላት በማሰማራት ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሌላኛው መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት በየአካባቢው ሕገ-መንግስቱንና የፌደራል ስርዓቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሰፋፊ ክፍተቶች ይታዩ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በየክልሉ የሞግዚት አስተዳደሮች ተመድበው ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አደም ከለውጡ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል።

አቶ አደም በአንዳንድ አካባቢዎች የተዛቡ ትርክቶችን መነሻ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቦችን እያጋጩ መሆኑንም ይገልጻሉ።

እነዚህም ማንነትን፣ ብሔርንና ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሕዝቦች ወንድማማችነት ላይ የራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉም ነው ያሉት።

በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶችም ነገሮችን ከየአካባቢያቸው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ሰፋ አድርገው ማየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አፈጉባዔው ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.