Fana: At a Speed of Life!

መላው ኢትዮጵያውያን በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት መረባረብ አለባቸው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መላው ኢትዮጵያውያን በመተባበር አሸባሪው ህወሃትን በመመከት ያስገኙትን ስኬት በቡድኑ የወደሙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እንዲረባረቡ ተጠየቀ።
የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በባህርዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የፓርቲው የክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ፥ አሸባሪው ህወሃት ካደረሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ ልቦና ጉዳት በፍጥነት በመውጣት ወደተሻለ ከፍታ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ቡድኑ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ መስሪያ ቤቶችን፣ ህብረተሰቡ የሚገለገልባቸው መሰረት ልማቶችንና የግል ድርጅቶችን በመዝረፍ ብሎም በማውደም ከጥቅም ውጭ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ወቅት የሰው ሃይል፣ ስንቅና ሌሎች ድጋፎችን አድርገው አሸባሪውን በመመከት ያስገኙትን አኩሪ ስኬት የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ላይ ለመድገም እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።
“ኢትዮጵያን የማትደፈርና ሉአላዊነቷ የተከበረ ለማድረግ ብዙ ስራ ይጠይቀናል፤ ሀገራችንን ጠንካራ የማድረግ ስራ መጀመር ያለብን ዛሬ ነው“ ብለዋል አቶ ግርማ።
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎችን ከበፊቱ የበለጠ ጥራትና ፍጥነት በመጨመር ጠንካራ አድርጎ በመገንባት የታፈረች ሀገር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም በየደረጃው ያለው ከፍተኛና መካከለኛ አመራር ሁሉን አቀፍና አዲስ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችል የስራ ስምሪት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
አመራሩ በተሰጠው ሁለንተናዊ ተልዕኮ ወደ አካባቢው ሲመለስ የተገኘውን ስኬት ለማስጠበቅና ለማስፋት የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ እንዳለበት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጠንካራ ፓርቲ፣ መንግስት፣ የህግ አስከባሪ አካላትንና የህዝብ አደረጃጀትን ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አደረጃጀቱም እንደ የሁኔታው የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ በልማት ስራዎች፣ በመልሶ ማቋቋምና ክልሉን ብሎም ሀገርን በማስጠበቅ ሁሉ እያዟዟርን ልንጠቀምበት የሚያስችል መሆን አለበት ሲሉም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.