Fana: At a Speed of Life!

መርማሪ ቦርዱ በህግ ማስከበር ዘመቻው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጐችን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በትግራይ ክልል በተካሄደው በህግ ማስከበር ዘመቻ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጐችን ጎበኘ።

ከሀዲው የህወሓት ቡድን ባደረሰባቸው ጥቃት በጎንንደር ከተማ ተጠልለው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦች እንዲሁም በአካባቢው ሲኖሩ የነበሩ ሌሎች ተፈናቃዮችን መርማሪ ቦርዱ አነጋግሯል።

ከተፈናቃዮቹ መካከል 80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት ሲሆኑ፥ የደረሰባቸው ጥቃት ያልገመቱት በመሆኑ አሰቃቂ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልጸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችና የከተማ መስተዳድሩ እያደረጉላቸው ላለው እንክብካቤም አመስግነዋል።

በተመሳሳይ ትግራይ ክልል ከሚገኝ የስደተኞች ካምፕ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ኤርትራውያን ስደተኞችም ስለተደረገላቸው እንክብካቤ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችንና መስተዳድሩን አመስግነው፤ በቀጣይ ግን አዲስ አበባ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የመርማሪ ቦርዱ አባላት ተፈናቃዮቹን ካበረታቱ በኋላ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አካላት መልዕክት በማስተላለፍ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በማይካድራ ከተማ የመስክ ምልከታ ያደረገ ሲሆን፥ በከተማዋ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ስለተፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል መረጃ ሰብስቧል።

የመርማሪ ቦርዱ አባላት ከ50 እስከ 60 አስከሬኖች በአንድ ላይ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፥ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ቀደም ሲል በተለያዩ ሚዲያዎችና የሰብአዊ መብት ተቋማት ከተጠቀሰው ሊያሻቅብ እንደሚችልም ታውቋል።

“ሳምሪ” የተባለው የወጣቶች ቡድን አሰቃቂ ወንጀሉን ቢፈጽምም፤ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች በመደበቅ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲተርፍ ማድረጋቸውን መርማሪ ቦርዱ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የመርማሪ ቦርዱ አባላት ተጎጂዎቹ በብዛት በሚኖሩበትና በተለምዶ “ግንብ ሰፈር” በተባለው አካባቢ ተገኝተው ከሟች ቤተሰቦችና ከግድያ ሙከራው ከተረፉ ሰዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ፥ ከጉዳቱ ሰለባዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት የጉዳቱን ኢሰብኣዊነት ገልጸው፤ መንግስት ወንጀለኞቹን አድኖ ለፍርድ እንዲያበቃ ለማገዝ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የቦርዱ አባላት በማይካድራ በነበራቸው ቆይታ በግድያ ወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን መጎብኘታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.