Fana: At a Speed of Life!

መስቀል አደባባይን በዘመናዊ መልኩ መልሶ ለማልማት ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መስቀል አደባባይ ለህዝባዊ አደባባይነት በሚመጥንና በዘመናዊ መልኩ መልሶ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከመስቀል አደባባይ ማዘጋጃ ቤት ደረስ የሚካሄደው መልሶ ማልማትና የአረንጓዴ ስፍራ ግንባታ ቅድመ ዝግጅት ያለበትን ደረጃ በዛሬው እለት ተመለክተዋል።

ለመልሶ ማልማቱና አረንጓዴ ስፍራ የቦታ ዝግጅትና የወሰን ማስከበር ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በጋራ ዝግጅቱን ተመልክተዋል።

በመስቀል አደባባይ መልሶ ግንባታ ቦታው ለህዝባዊ አደባባይነት በሚመጥን መልኩ በዘመናዊ መልኩ የሚገነባ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ቦታው ላይ ከመሬት በታች እስከ 1400 ተሽከርካሪ ለማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ይገነባል።

ፋውንቴንና የተለያዩ መዝናኛዎችን ባካተተ መልኩ የሚገነባው መስቀል አደባባይ መልሶ ግንባታው በለገሀር ቸርችል አደባባይ እስከ ፒያሳ ድረስ በሚሰራው አረንጓዴ ስፍራ ፕሮጀክት ጋር የተያያዘ ነው።

ከመስቀል አደባባይ እስከ ፒያሳ ድረስ ያለው መንገድ ትይዩ በሆነ መልኩ የሚገነባ ሲሆን በመንገዶቹ ጠርዝ ያለው የእግረኞች መሄጃ ሰፋ ባለ መልኩ የሚገነባ መሆኑም ታውቋል።

የመንገዶቹ ጠርዝ ለአካል ጉዳተኞች እንዲመች ተደርጎ እንዲሁም የብስክሌት መጓጓዧን ባካተተ መልኩ እንደሚገነባም ነው የተገለፀው።

ፕሮጀክቱ ዲዛይኑ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርብ ወደ ስራ የሚገባ ሲሆን፥ በቀጣይም ይህን እንደመነሻ በመውሰድ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የማስዋብ ስራዎች የሚተገበሩ መሆኑ ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.