Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን ያሳለፈው ግጭት የማቆም ውሳኔ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዲሳለጥ አድርጓል – ተመድ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን ያሳለፈው ግጭት የማቆም ውሳኔ በትግራይ ብቻ ሳይሆን ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲፋጠን አስችሏል ሲል የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት (ተመድ) ገልጿል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ተጠሪና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ለኢዜአ እንደተናገሩት÷ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ያሳለፈው ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል።

ይህንንም ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን ግጭት በተከሰባቸው አካባቢዎች የሚደርሰውን ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፎች በየብስና በአየር ተደራሽ እንዲሆን ሰፊ ዕድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰኑ አማራና አፋር ክልሎች ድንበር አካባቢዎች በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን የነፍስ አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሳለጥ እንዳስቻለም ተናግረዋል፡፡

ውሳኔው በችግር ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁሳቁሶችን ተደራሽ ለማድረግ ከማስቻሉ ባሻገር ጥሬ ገንዘብና ነዳጅም ለማጓጓዝ እንዳስቻለ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ተሰብስቦ ወደ ክልሉ የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንሰራለን ብለዋል ዶክተር ካትሪን።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.