Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ስር የሰደደውን ሌብነት ለመቆጣጣር ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ የመንግስት አስተዳደር ለብዙ ጊዜ ስር የሰደደውን ሌብነት ለመቆጣጣር ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የህግ እና የፀረ ሙስና የማህበረሰብ አንቂ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፀረ ሙስና የማህበረሰብ አንቂና የህግ አማካሪው አቶ ክብረ አብ አበራ÷ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ባለስልጣናት በተሳተፉበት ሁኔታ በሚፈጸም ሌብነት በርካታ የሀገር ሀብት ተዘርፏል ።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ሀይሉ ነጋ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት÷ ከግዙፉ ስርቆት እስከ አገልግሎት አሰጣጥ በደል የደረሰው የሌብነት ተግባር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በመንግስት ስራ ተቀጥሮ ደመወዝ የሚከፈለው ሰራተኛ ጭምር በዚሁ የሀገር ሀብት ስርቆት ውስጥ ተሳታፊ ነበር ያሉት አቶ ሀይሉ ነጋ ÷ በሁሉም ዘርፎች የተንሰራፋው ስርቆት በአዲስ ምዕራፍ ወደ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚንደረደረውን ጉዞ እንዳይፈትን የምዝበራ ሰንሰለቱን ለመቆጣጠር አዲሱ አስተዳደር በትጋት መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ሁሉም አካላት ሌብነትን ለማጥፋት ተግባራዊ ጥረት ማድረግና ሀገራችን በሀብቷ እንድትለወጥ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ስር የሰደደውን ሌብነት ለመቆጣጠር የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፣ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቶችም መጠናከርና ራሳቸውን ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ አድርገው መንቀሳቀስ በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲሱ መንግሥት የተካተቱ ሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዴኤታዎች በዚህ ሳምንት በተጀመረው የሥራ ማስጀመሪያ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በአገልጋይ መሪነት ልብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስሳበው፥ የዚህች ታላቅ ሀገር ዜጎች ከዚህ ያነሰ አገልግሎት አይገባቸውም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በሀይለየሱስ መኮንን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.