Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ ክልል ህይወት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል ህይወት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ከዓለም አቀፍ ለጋሽና አጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም አሁን ላይ በክልሉ ያለው እንቅስቃሴ ወደቀደመ ሁኔታው እንዲመለስ በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በክልሉ ከተካሄደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም አሁን ላይ የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት በክልሉ ያለገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እየደረሱ መሆኑን የጠቀሰው ፅህፈት ቤቱ እስካሁን ለ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ ተችሏል ነው ያለው፡፡

ከሰብአዊ ድጋፉ ባለፈም መንግስት በክልሉ ያለውን የፀጥታ፣ ሰብአዊ እና ማህበራዊ ተግዳሮቶች ለመፍታትና እንቅስቃሴዎች ቀድሞ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

በክልሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስም ከሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አውስቷል፡፡

መንግስት የተረጋጋች፣ ሰላማዊ እና ለነዋሪዎች የምትመችን ትግራይ ለመገንባት ቁርጠኛ ነውም ብሏል፡፡

መግለጫው ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን አንስቷል፡፡

ይህን ተከትሎም መንግስት ጽንፈኛውን ቡድን ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በክልሉ በማረሚያ ቤት የነበሩና በጽንፈኛው ቡድን የተለቀቁ ከ10 ሺህ በላይ ታራሚዎች ፈጽመውታል የተባለውን ወንጀል ጨምሮ በክልሉ አሉ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርመራና ማጣራት እየተደረገባቸው መሆኑንም አስታውሷል፡፡

በምርመራው የሚገኘውን ውጤት ተከትሎም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳልም ነው ያለው መግለጫው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.