Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል ተብሎ በቀረበው ውንጀላ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል ተብሎ ለቀረበው ውንጀላ ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው የቀጠናውም ሆነ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጀ ብሊንከን በትግራይ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል የሚል ውንጀላ ማቅረባቸውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል፡፡

በቀረበው ውንጀላ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ መንግስት አለ ለተባለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ሂደት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን ሰብአዊ መብት እንደምታከብርና ግዴታዋን እንደምትወጣ ያነሳው መግለጫው፥ በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ንጹሃንና ተቋማትን ከጥቃትና ጉዳት መጠበቅ ባስቻለ መልኩ መከናወኑንም ጠቅሷል፡፡

ከዚህ ባለፈም መንግስት ሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የሚቀርቡ ውንጀላዎችን በአጽንኦት እንደሚመለከት በመጥቀስ፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ አሉ የተባሉ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራትና ተሳትፈዋል የተባሉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ አስፈላጊውን ማጣራት እያደረገ ስለመሆኑም አውስቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ ቡድን አለ ከተባለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ሁኔታዎችን የማጣራት ስራ በክልሉ እየሰራ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የማይካድራውን ጭፍጨፋ ጨምሮ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችን በተመለከተ ማጣራት ማድረጉን እና በዚህ ሂደት የደረሰባቸውን ቀዳሚ ግኝቶችን ይፋ ማድረጉንም ጠቁሟል፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያቀረቡት ውንጀላ መሬት ላይ የሌለ እና ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መሆኑንም መግለጫው አንስቷል፡፡

መንግስትም ተፈጽሟል ለተባለው ማንነትን መሰረት ያደረገ የጥቃት ውንጀላ ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካባቢያዊም ሆኑ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትና አጣሪ ባለሙያዎች ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አስታውቋል፡፡

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በጉዳዩ ላይ ከዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ ስለመዘጋጀቱም ነው የገለጸው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.