Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ መንገድ ትተው ሊዋጉን ለሚከጅሉ ሃይሎች በአጭር ጊዜና በማያዳግም ሁኔታ በምንወስደው ወታደራዊ እርምጃ አገራችንን ዳግም የምናስከብርበት ዝግጅት አጠናቀናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ መንገድ ትተው ሊዋጉን ለሚከጅሉ ሃይሎች በአጭር ጊዜና በማያዳግም ሁኔታ በምንወስደው ወታደራዊ እርምጃ አገራችንን ዳግም የምናስከብርበት ዝግጅት ማጠናቀቃችንን ለሚመለከተው ሁሉ እናሳውቃለን ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ ይህን ያሉት የ8ኛ ደቦል ዕዝ የሜዳይና የዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚሁ ንግግራቸው÷ ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላምን ማረጋገጥ፣ ተቻችሎና ተስማምቶ አስተማማኝ ቀጠናዊ ሰላም በጋራ የማስፈን መርህ በመከተል የሰላም አማራጮችን ሁሉ እንጠቀማለን ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ህወሓት ባልዋለበት ገድል ራሱን የሚያፅናና እና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሸንፎ እያለ÷ አንድ ውጊያ ላይ ድል ቀናኝ በሚል ውጊያውን ሲያንቆለጳጵስ የሚውል ድል የጠማው ኃይል መሆኑንም አውስተዋል፡፡
መንግስት ለሰላም የሚዘረጋውን እጅ እንደግፋለን ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ ነገር ግን መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ መንገድ ትተው ሊዋጉን ለሚከጅሉ ሃይሎች በአጭር ጊዜና በማያዳግም ሁኔታ በምንወስደው ወታደራዊ እርምጃ አገራችንን ዳግም የምናስከብርበት ዝግጅት ማጠናቀቃችንን ለሚመለከተው ሁሉ እናሳውቃለን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ታሪካዊ በሆነው የሃገርን ሉዓላዊነት የማስከበርና የሃገርን ህልውና ለማቆየት ከጠላት ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ ካደረጉ የሰራዊት ክፍሎች መካከል÷ አንዱ ስምንተኛ ዕዝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስምንተኛ ዕዝን ስናደራጅ ሀገራችን የነበረችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ወደ ውስጥ የዘለቀውን የህወሓት ወራሪ ሃይል ከገባበት መውጣት እንዳይችል ለማድረግ ታቅዶ በነበረው ዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሰራዊታችን ጠንካራ ክንድ ሆኖ እንዲያገለግል በማቀድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ስምንተኛ ዕዝ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሰጠው ጊዜና ቦታ በላቀ ጀግንነት በመፈፀም የኢትዮጵያን ህዝብ ያኮራ ባለውለታ ለመሆን ችሏል ብለዋል።
በሃገራችን ላይ አንዣብቦ የነበረው የመፍረስ አደጋም በስምንተኛ ዕዝ አመራርና አባላት ቆራጥ ተጋድሎ ጭምር መወገዱን ጠቁመው÷ ”በገድላችሁ ላተማችሁት አሻራ ምልክት ይሆን ዘንድ ይህ ሜዳይ ተበርክቷል” ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.