Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የዜጎችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 ኤፍ.ቢ.ሲ) የዜጎች መከበር የሃገር መከበር መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የዜጎችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ የዓረብ ሀገራት ለተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በዱባይ አል አህሊ ስታዲየም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሊባኖስ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታር እና ባህሬን የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያውያኑ በፈተና ህይዎት ውስጥ ሆነው ለሃገራቸው እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

መንግስትም የዜጎች መብት ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማድረግ ከየሀገራቱ መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አድርጓልም ነው ያሉት።

የዜጎች መከበር የሃገር መከበር መሆኑን በመገንዘብም የዜጎችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋልም ብለዋል በመልዕክታቸው።

ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት ነበር የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የገቡት።

በቆይታቸውም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ትናንትናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተውጣጡ ከ250 በላይ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.