Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ ሁለት ዕዞችን አደራጀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚሰጠኝን ግዳጅ በፍጥነት ማከናወን ያስችሉኛል ያላቸውን ተጨማሪ ሁለት ዕዞች ማደራጀቱን አስታወቀ።

አዲሶቹ ዕዞች በዚህ ዓመት ወደ ስራ እንሚገቡም ነው የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የገለጸው።

የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ እና የሠራዊቱ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጦር ኃይል አዛዦቹ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የለውጥ ስራዎች፣ በሠራዊቱ አደረጃጀትና በወቅታዊ የሠላምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሠራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በፍጥነት ማከናወን እንዲችል ሁለት አዳዲስ ዕዞች መደራጀታቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ዕዞቹ በውስጥም በውጭም የሚቃጡ ጥቃቶችና ችግሮችን ፈጥነው ለመከላከል እንዲችሉ ታስቦ የተደራጁ ናቸው ብለዋል።

ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ አዲስ የተደራጁት ዕዞች ሲሆኑ የቀደሙት ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምስራቅ ዕዞች መኖራቸውንም አውስተዋል።

አዲስ የተደራጁት ዕዞች በተያዘው ዓመት ወደ ስራ እንደሚገቡም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.