Fana: At a Speed of Life!

መገለል በህጻናት የጭንቅላት መጠን ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ልጆችን ከማህበረሰብ አግልሎ ማሳደግ በጭንቅላት መጠን እድገታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አንድ ጥናት አመላከተ።

መገለል፣ በአስቸጋሪና ፈተና የተሞላ ህይወት ማሳለፍ በልጆች የጭንቅላት መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በለንደን በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ የተካሄደ ጥናት አመላክቷል።

ጥናቱ በተለያዩ ተቋማት በጉዲፈቻ በሚያድጉና አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከማህበረሰቡ ተነጥለው በሚያሳልፉ ህጻናት ላይ የተደረገ ነው።

ጥናቱ በዚህ መልኩ የሚያድጉ ህጻናት በወጣትነት ዘመናቸው የሚኖረው የጭንቅላት መጠን የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት ካላቸው ህጻናት አንጻር ሲታይ እንደሚቀንስ ያመላክታል።

በጥናቱ መሰረት ብዙም ማህበራዊ ግንኙነት የሌላቸውና ከማህበረሰቡ ተገለው የሚቆዩ ህጻናት የጭንቅላት መጠናቸው በ8 ነጥብ 6 በመቶ ይቀንሳል ነው የተባለው።

ለዚህ የተጋለጡት ህጻናት ብዙ ጊዜያቸውን በብቸኝነትና ያለምንም አይነት መጫወቻ የሚያሳልፉ መሆናቸውን የጥናት ቡድኑ ገልጿል።

በጥናቱ የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት ባላቸውና በሌላቸው ህጻናት መካከል በሶስት የጭንቅላት ክፍሎቻቸው ላይ ልዩነት አይተናልም ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ።

ይህም አዕምሮ ነገሮችን በሚያደራጅበት፣ የነገሮችን ፍሰት በሚወስንበት፣ ያገኛቸውን መረጃዎች በሚያቀናጅበትና በሚያስታውስበት ክፍል ላይ የአወቃቀር ልዩነት መኖሩንም አስረድተዋል።

ይህ ደግሞ ህጻናቱ ዝቅተኛ የማገናዘብ ችሎታ እንዲኖራቸው፣ ለኦቲዝም፣ መቅበጥበጥና አለመረጋጋት እንዲሁም ለትኩረት ማነስና ፍርሃት ተጋላጭ ያደርጋቸዋልም ብለዋል።

ሁኔታው በአካል እና ስነ ልቦና እድገት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውም የቡድኑ አባላት ገልጸዋል።

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.