Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን የሕዳሴ ግድብ መረጃዎችን በሚጠበቅባቸው ልክ  በመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ብዙሃን ስለ ሕዳሴ ግድብ ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝቡና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በሚፈለገው ልክ በመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤትና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ‘የመገናኛ ብዙሃን ሚና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ’ በሚል መርህ የምክከር መድረክ አካሂደዋል።

የግድቡ አሁናዊ የአፈጻጸም ደረጃና ይህን ተከትሎም ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዴት ሊወጡ ይገባል የሚሉ ሀሳቦች ተነስቷል።

የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ÷ መገናኛ ብዙሃን ከምን ጊዜውም በላይ ስለ ሕዳሴ ግድብ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የኢኮኖሚ ነጻነት ጉዳይ ነው” ያሉት ዶክተር አረጋዊ በዚህ ረገድ ሚዲያው መርህን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር በመጫወት ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ወንደሰንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሊካሄድ በመሆኑ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን መቆጣጠር የሚያስችል የመረጃ ስርጭትና ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሂደቱ እንዳይሳካ የሚሹ ሃይሎች በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር በበይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች እየሰሩ መሆኑንም አንስተው÷ይህን ለመቀልበስና በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍያለ መሆኑን ገልጸዋል።

በተፋሰስ ልማት ባለስልጣን የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ተመስገን በበኩላቸው ÷ በግድቡ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እንዲሳኩ ሚዲያው የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አንስተዋል።

የኢትዮጵያን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ አካሄድ ለዓለም ማስረዳት ይኖርበታልም ብለዋል።

በመድረኩ ባለድርሻ አካላትና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን  መሳተፋቸውን  ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.