Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በሦስተኛ ዲግሪ በትብብር የሚሰጡ አገር በቀል የትምህርት ፕሮግራሞችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሦስተኛ ዲግሪ በትብብር የሚሰጡ አገር በቀል የትምህርት ፕሮግራሞችን ይፋ አደረገ።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በምርምር እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች 5 ሺህ ተማሪዎችን በ3ኛ ዲግሪ ለማሰልጠን መታቀዱንም አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በሦስተኛ ዲግሪ በትብብር የሚሰጡ አገር በቀል የትምህርት ፕሮግራሞችን ዛሬ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት አስተዋውቋል።

በዚህም የትምህርት ፕሮግራሞቹ በግብርና ፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሊጂ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው በተዘጋጀው ይፋ ማድረጊያ መርሃ-ግብር ላይ ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚህ ወቅት እንዳሉት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በምርምር እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች 5 ሺህ ተማሪዎችን በ3ኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር ለማሰልጠን ታቅዷል።

በሦስተኛ ዲግሪ በትብብር ለሚሰጡ አገር በቀል የትምህርት ፕሮግራሞች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ ሀብት፣ መሰረተ ልማት እና ቁሳቁስ በጋራ መጠቀም እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ስልጠናው በትብብር መሰጠቱ ተማሪዎቹ ከሱፐርቫይዘሮች፣ ከአማካሪዎች እና በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ካሉ ጓደኞቻቸው ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚያስችላቸውም ነው ዶክተር ሳሙኤል ያመለከቱት።

ሚኒስትሩ በአገሪቱ የትምህርት ልማት አግባብነትና ጥራትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል።

“የሳይንስ ልማትን በኢትዮጵያ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፣ በአገሪቱ ለምርምር ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የአገሪቱን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀምና ለአገር ዕድገት ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

“በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮችን ወደ ተግባር በመቀየር ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል” ብለዋል።

የመምህራን ልማት ለትምህርት ጥራት ቁልፍ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት ይሰራበታል።

በ3ኛ ዲግሪ በትብብር በሚሰጡ አገር በቀል የትምህርት ፕሮግራሞች በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ በርካታ ተማሪዎችን ለማሰልጠን ብቁ የሆኑ መምህራንን ማፍራት አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ለዚህም ሚኒስቴሩ በ10 ዓመት መሪ እቅዱ የተቋማትን አቅም ለመገንባትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለያዩ ተቋማት የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀም፣ ከሌሎች ጋር በቅንጅት በመስራትና፣ የሃብት ብክነትን በመከላከል ለአገሪቱ ልማት በትኩረት መስራት ተገቢ መሆኑንም አሳስበዋል።

የትምህርት ፕሮግራሞቹን ለማሳካት ተቋማት ያዘጋጁትን ስራትራቴጂክ እቅድ በስራ ላይ ማዋልና በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትኩረት መስክና በልህቀት ማዕከል ልየታ መሰረት የምርምር እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በሚል ከተለዩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባምንጭ ፣ ባህርዳር ፣ ሀሮማያ፣ ሃዋሳ ፣ ጅማ ፣ መቀሌና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙበት እንደሚገኙበት ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.