Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር የ600 ሺህ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መርሀ ግብር ማስፈጸሚያ የሚውል የ600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።

የድጋፍ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ ላሰበችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የሚያግዝ  ነው ተብሏል።

የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የተፈረመው ገንዘቡ ጥቅም ላይ በሚውልበት ሁኔታ ላይ ሚኒስቴሩ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ጋር  ውይይት ካደረገ በኋላ  መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ፥ የዲጂታል ሂደቱ አጠቃላይ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማቃለል የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም  “የዲጂታላይዜሽን” ሂደቱ በዚህ ወቅት ዓለምን እየመራት  ነው  በመሆኑ ሂደቱ ገበያን ለማቀላጠፍ፣ ትምህርትን እና ህክምናን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ያዘምናል  ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ ሂደቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረጉ መንግስት የበለጠ ለዜጎች እንዲቀርብ የሚያደርግ ሲሆን፥ ዜጎች ቤት ሆነው አገልግሎት የሚሰጡበትና ግልጋሎት የሚያገኙበትን ዕድል ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.