Fana: At a Speed of Life!

ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ኒሻን ጨምሮ አራት  የቀድሞ የጦር መኮንኖች  በህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን አመራሮች  ተገደው  ሚኒሻዎችን ሲያደራጁ እንደነበር ለፍርድቤት ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ   ለአገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ኒሻን ጨምሮ  አራት  የቀድሞ የጦር መኮንኖች  በህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን አመራሮች  ተገደው  ሚኒሻዎችን ሲያደራጁ እንደነበር ለፍርድ ቤት ገለጹ

ተጠርጣሪ የጦር መኮንኖቹ ይህን ያሉት  በዛሬው እለት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ነው።

ፍርድቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ  ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ኒሻ ፤ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ በርሄ፣  ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ሚካኤል እና ኮሎኔል ገብረዋሕድ ኃይሉ  ናቸው ።

ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ያቀረበው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን  የተጠረጠሩበትን የወንጀል  ጉዳይ ለችሎት ይፋ አድርጓል።

በዚህም የሕወሓት ጸረሰላም  የጥፋት ቡድን ከፍተኛ አመራሮችና ከኦነግ ሸኔ  የጸረ ሰላም ቡድን ጋር በመቀናጀት  ከቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ተልኮ በመቀበል የትግራይ ልዩ ሃይልን በማደራጀት፣ በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት እንዲደርስ እና የእዙ ጦር መሳሪያ እንዲዘረፍ አድርገዋል ሲል አብራርቷል።

ከጦር መሳሪያውን ካዘረፉ  በኋላ ደግሞ እጃቸውን እስከሰጡበት ጊዜ ድረስ ጦርነቱን በመምራት ዜጎችን በማስጨፍጨፍ  ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ  ሙከራ ወንጀል  መጠርጠራቸውን ለችሎቱ  ፖሊስ ገልጿል።

ስለሆነም የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናክሮ  ለማቅረብ በስነ ስርአት ህጉ መሰረት 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል መርማሪ ፖሊስ  ተጨማሪ ቀናት  ጠይቋል።

1ኛ ተጠርጣሪ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ኒሻ በበኩላቸው÷  ለራሳቸው ሰግተው ከመቀሌ መውጣታቸውን እና ተሸሽገው እንደነበር በመግለጽ  በቤተሰብ አማካኝነት አክሱም ለሚገኝው መከላከያ ሃይል ሪፖርት አድርገው እጃቸውን እንደሰጡ ተናገረዋል።

ከቤተሰብ ጋር ተማክረው ጠበቃ እንደሚያቆሙ በመጠቆም የጡረታ አበል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

2ኛ ተጠርጣሪ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ በርሄ በበኩላቸው ÷አክሱም ላይ እራሳችን ነን እጃችንን የሰጠነው የመኖሪያ አድራሻዬ እዚህ ነው የጡረታ አበል እንዲሰጠኝ ይፈቀድልኝ የዋስትና መብቴም ይከበርልኝ ሲሉ የዋስትና ጥያቄ አነስስተዋል።

3ኛ ተጠርጣሪ ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ሚካኤልም የህዋት ቡድን አመራሮች አስገድደውኝ ነው ሚኒሻዎችን  ሳሰባስብ የነበረው የታዘዝኩትን ሚኒሻ የማሰባሰብ ስራ ከጨረስኩ በኋላ ከተሸሸግሁበት በመውጣት ወደ ጄኔራል ዮሀንስ ስልክ በመደወል መቀሌ  በመሄድ ራሴ እጄን ሰጥቻለው  ሲሉ ለፍርድቤቱ አብራርተዋል።

4ኛ ተጠርጣሪም  ኮሎኔል ገብረ ዋሕድ ኃይሉ በወቅቱ ስጋት ሰለነበረብን ጫካ ወስጥ ተደብቀን ቆይተን ነው እጃቸንን የሰጠነው ሲሉ ለችሎቱ አያያዛቸውን ገልጸዋል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ክርክሩን አዳምጦ ለፖሊስ  14 ተጨማሪ ቀናተን ፈቅዶለታል።

ተጠርጣሪዎቹን  የአገር መከላከያ ሠራዊት ባሳለፍነው  ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለፌዴራል ፖሊስ ማስረከቡ ይታወሳል ።

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.