Fana: At a Speed of Life!

ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም እየተደረገ ነው-የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ)ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ እና ባለሙያዎች እንዲሁም ሞዴል አርሶ አደሮች በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በክላስተር የተዘራ የጤፍ እና ስንዴ ማሳን ጎብኝተዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ልየው እንደገለጹት፥ በዞኑ በአሁኑ ወቅት 602 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 22 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ያሉት ሃላፊው፥በዚህም በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲተገብሩ መደረጉን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በሁለት እጁ ነሴ ወረዳ በክላስተር የተዘራ የስንዴ እና ጤፍ ማሳ ላይ ፀረ አረምና ፀረ ዋግ ኬሚካል ለሙከራ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

‘ፓላስ ሱፐር’ የተሰኘው ፀረ አረም ኬሚካል በስንዴ እና ጤፍ ማሳ ላይ የሚወጣውን አረም ሙሉ በሙሉ በማስቀረት የአርሶ አደሮችን ድካም መቀነሱን ነው የገለጹት።

በአረም ምክንያት የሚከሰተውን የምርታማነት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም ጸረ አረም ኬሚካሎችን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤፍ እና ስንዴ ፀረ አረም እና ፀረ ዋግ ኬሚካል ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፥ ኬሚካሉ ጤፍ እና ስንዴ የዘሩት ማሳ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉን አንስተዋል።

ጤፍ እና ስንዴ ከተዘራ በኋላ የሚወጣውን አረም ለመንቀል ብዙ የሰው ሃይልና ጊዜ ያባክኑ እንደነበር የገለጹት÷ አርሶ አደሮቹ፥የተጠቀሙት ፀረ አረም ይህንን ችግር እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ኬሚካሉ የተዘራው የጤፍ እና ስንዴ ማሳ ላይ ምንም አይነት አረም እንዳይበቅል የሚያደርግ በመሆኑ ምርታማነቱን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.