Fana: At a Speed of Life!

ምርጫና የሴቶች የነቃ ተሳትፎ በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምርጫና የሴቶች የነቃ ተሳትፎ በሚል የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት ኮሚሽነር ወይዘሮ መሠረት ማሞ÷ ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ በሌሎች ዝርዝር ህጎችና ፖሊሲዎች ማካተቷን ተናግረዋል።

በመሆኑም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 38  ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በጾታ ወይም በሌላ ልዩነት ሳይደረግ የመምረጥ መብት እንዳላት/እንዳለው ይደነግጋል ብለዋል።

በምርጫ ወቅት በማሕበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎችም በአካልና በስነልቦና ላይ ጫና የሚያሳድሩ ዘርፈ ብዙ ፆታዊ ጥቃቶች ሴቶች በዕጩነት፣ በምርጫ ሥራ አመራርነት ከላይ እስከታች ወደ መድረክ እንዳይወጡ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደራቸውንም አንስተዋል፡፡

ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውንም ሆነ የዜግነት መብታቸውን ከመጠቀም አንጻር ተንሰራፍቶ ባለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት ጫና እንደሚደርስባቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም እንደሃገር ዴሞክራሲን ለማበልጸግና ማንንም ወደኋላ ባለማስቀረት ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት የሚደረገውን ጥረት እንደሚገድብ አውስተዋል፡፡

ሴቶች በቀጣዩ ምርጫ በሀገራቸው የውሳኔ ሰጪነት መድረክ በተገባቸው መጠን በመሳተፍ በዴሞክራሲና የሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ ባለቤትና አካል እንዲሆኑ እንዲሁም ፓርቲዎች የሴቶችን አባልነት በማጠናከር አጀንዳዎቻቸውንም የማካተት ድርሻቸውን እንዲወጡ፤ የሲቪል ማሕበራትም ምርጫው ለስርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

በመድረኩ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በኢትዮጵያ፣ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች፣ በምርጫ ሒደት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ በምርጫ ሒደት የሴቶችን ተሳትፎ እና ውክልና ማሳደግ እና የምርጫ ሒደት ለስርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ እንዲሆን የሚዲያ አስተዋጽኦ በሚሉ ጥናቶች ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በዘመን በየነ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.