Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ ለብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ውሳኔ አሳለፈ።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲዎች ምዝገባ ጥያቄዎች ዙሪያ የተለያዩ ውሳኔዎችን በዛሬው እለት አሳልፏል።
 
ቦርዱ የእውቅና ጥያቄ እና የፓርቲ መለያ ሰንደቅ አላማ የማጸደቅ ጥያቄን ያቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ በመመልከት ውሳኔ ማሳለፉንም ነው ዛሬ የገለፀው።
 
የኢህአዴግ አባል የነበሩ ሶስት ፓርቲዎች እና ሌሎች አምስት ፓርቲዎች በጋራ ራሳቸውን በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን መመስረታቸውን በማሳወቅ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው ህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጥያቄ ማቅረባቸውን ቦርድ አስታውሷል።
 
ቦርዱም ጥያቄውን በፓለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ 1162/2011 መሰረት መርምሮ ውሳኔ ማሳለፉን ነው የገለጸው።
 
ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ተጨማሪ መሟላት ያለባቸውን ሰነዶች ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሟሉ መጠየቁን ነው የገለፀው። ታህሳስ 06 ቀን 2012 ዓ.ም የጥያቄዎቹ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ ብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት፦
 
  • የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ፣
  • የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን)፣
  • የሃረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣
  • የአማራ ዴሞክራያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) ፣
  • የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ)፣
  • የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) እና
  • የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋህአዴን) እና
  • የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)
 
በተናጠል በጠቅላላ ጉባኤያቸው ውሳኔ መሰረት አድርገው ውህደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም የወሰኗቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ውህደቱን ለመመስረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ህጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው መወሰኑን አስታውቋል።
 
በዚህም መሰረት ውህዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሰረት በተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ያስገኘውን ሃብትና ንብረት እና እዳ የሚያሳይ የሂሳብ ሪፓርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ በቦርዱ ውሳኔ ውስጥ መካተቱን ነው ያመለከተው።
 
በሌላ በኩል የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ በምዝገባ ወቅት ያቀረበው ሰንደቅ አላማ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ይመሳሰላል በሚል በቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይመሳሰል በመግለጽ ልዮነቱን አብራርቶ ቦርዱ እንዲቀበለው ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል።
 
ቦርዱም በሁለቱ ሰንደቅ አላማዎች መካከል አለ የተባለውን ልዩነት መርምሮ የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ የጠቀሳቸው ልዮነቶች ለማስተዋል የሚያስቸግሩ በመሆናቸው እና ድምጽ ሰጭዎችን የሚያምታታ ሆኖ በመገኘቱ ሰንደቅ አላማውን ቀይሮ በማቅረብ ምዝገባውን እንዲያጠናቅቅ ውሳኔ ሰጥቷል።
 
እናት ፓርቲ በሚል አገር አቀፍ ፓርቲ ለማቋቋም በሂደት ላይ ያለ ፓርቲ በአዋጅ 1162/ 2011 መሰረት ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡን የገለፀው ቦርዱ፥ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን ጊዜያዊ ሰርተፍኬት መውሰጃ መስፈርት በሟሟላቱ እናት ፓርቲ የጊዜያዊ እውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ውሳኔ ማሳለፉን ቦርዱ አስታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.