Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ ምርጫ መታዘብ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ መታዘብ ሥራ መሳተፍ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ፡፡

ቦርዱ በኢፌዴሪ ህገመንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ቦርዱን ባቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ነው ጥሪውን ያቀረበው፡፡

በዚህም ምርጫ ለመታዘብ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ለመስጠት እና ለመከታተል የሚያስችለውን መመሪያ አርቅቆ፣ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወኪሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ያገኘውን ግብዓት በማካተት፣ የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና የሥነ ምግባር መመሪያ ቁጥር 05/2012ን አፅድቋል፡፡

በዚሁም መሰረት በቀጣዩ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች መሳተፍ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ገለልተኛ ምርጫ እንዲኖር በማድረግ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በማመን መሆኑ ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

6ኛውን የሀገር-አቀፍ አጠቃላይ ምርጫ መታዘብ የሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥያቄያቸውን ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ይህንን ጥሪ ማድረግ ማስፈለጉንም ነው የገለጸው፡፡

በዚህ መሠረት ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ የመንግስት አካል ያልሆኑ እና በህግ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ፣ የተቋማቸው የቦርድ አባላት እና መሪዎች የማንኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ፣ የምርጫ መታዘብን ሥራ ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያላቸው እና የሚሰማሩት ታዛቢዎች ምርጫን በገለልተኝነት ለመታዘብ የሚችሉ፤ እንዲሁም ለምርጫ መታዘብ ሥራ በመመሪያው የወጡ ሌሎች መስፈርቶችን የሚያሟሉ  እና ምርጫ ለመታዘብ የምትፈልጉ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው አካላትም ለዚሁ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ፣ የታዛቢዎች ዝርዝር መረጃ ቅጽ እና ቃለ መሃላ በመሙላት የተጠየቁ ሰነዶችን በማያያዝ ማመልከቻቸውን ዋናው መስሪያ ቤት፣ ለምርጫ ቦርድ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ወይም በኢሜል አድራሻ externalrelations@nebe.org.et ይህ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኀን ከወጣበት ከቀን ከታህሳስ 02 ቀን 2013 ዓ.ም  ጀምሮ በ15 የስራ ቀናት ውስጥ  እንድታቀርቡ ቦርዱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የማመልከቻ ዝርዝር ቅጾቹን ከቦርዱ ድረ ገጽ www.nebe.org.et መመልከት እንደሚቻልም ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.