Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት የ160 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚውል የ160 ሺህ ዶላር እና 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የምክር ቤቱ ጸሐፊና የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ዳዊት ጋላሶ በተለያዩ ሀገሮች የሚኖረው ዳያስፖራ የሀገሩን ሁኔታ በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያን ለመበታተን በህወሓት ጁንታ በኩል የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች በዳያስፖራው ዘንድ ስጋት ፈጥረው እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይሁንና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ስኬታማ ሥራ መከናወኑ ኢትዮጵያዊያኑን ከስጋት እንዲወጡ ማድረጉን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ስድስት ወራት ያስቆጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፤ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ከ364 ሺህ ዶላር በላይ ማሰባሰቡን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥ 160 ሺህ ዶላር ዛሬ በመከላከያ ሚኒስቴር ተገኝተው ያስረከቡ ሲሆን ቀሪውን በአጭር ጊዜ እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት በአጭር ጊዜ ድጋፍ አሰባስበው አጋርነታቸውን በማሳየታቸው አድንቀዋል።

ዳያስፖራው ባለው ዕውቀትና ገንዘብ ለኢትዮጵያ ልማትና ገጽታ ግንባታ የተሻለ ሥራ አንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የዘሉሲ ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር ለመከላከያ ሠራዊት 85 ሺህ ብር አበርክቷል።

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ረታ ነግሬው “በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሀገር ከማጥፋት የማይተናነስ ነው” ብለዋል።

የማኅበሩ አባላት ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ያደረጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል መግባታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወይዘሮ ማርታ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ውጤታማ የሆነው በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ መሆኑን ገልፀው፤ በየቦታው የተበታተኑ የጁንታውን አባላት መልቀምና ክልሉን መልሶ የማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.