Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የሶስት ሚኒስትሮችን ሹመት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሶስት ሚኒስትሮችን ሹመት አፀደቀ።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
 
በመደበኛ ስብሰባው ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን የሶስት ሚኒስትሮች ሹመት አጽድቋል።
 
በዚህም ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር፣ አቶ መላኩ አለበል የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲሁም ዶክተር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ሹመትን አጽድቋል።
 
አዲስ የተሾሙት ሚኒስትሮችም በዛሬው እለት በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
 
ሚኒስትሮቹ ከጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተሾሙ ሲሆን፥ ሹመቱ በምክር ቤቱ ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት ይፋ መደረጉ የአካሄድ ችግር አለበት የሚል ሃሳብ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቶ ለቀጣይ እርምት የሚወሰድበት እንደሆነ ተገልጿል።
 
በመቀጠልም ምክር ቤቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀምን አድምጧል።
 
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የተቋሙን የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፥ በበጀት ዓመቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበረ አንስተዋል።
 
ከዚህ ውስጥ አዲስ መማሪያ መጽሃፍት ማዘጋጀትና የተማሪዎች ምደባ ህብረ ብሄራዊ እንዲሆን ማድረግን ጨምሮ ከተማሪዎች እና ከተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት ማድረግ እንዲሁም የቤተሰብ ውል ማስፈፀምን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
 
ሆኖም ግን ከህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግጭት መከሰቱን እና በግጭቱም የሰው ህይወት ማለፉን እንዲሁም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በሪፖርታቸው አንስተዋል።
 
ለግጭቶቹ መስፋፋት የአመራር ድክመት እንዲሁም የሚዲያው በተለይም ማህበራዊ የትስስር ገፆች የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨት የብሄር እና የሀይማኖት መልክ እንዲይዝ ማድረጋቸው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ከ1 ሺህ 200 በላይ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ የተለያየ መጠን ያለው እርምጃ ተወስዷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ 421 ተማሪዎች ላይ ከ1 ዓመት ቅጣት ትምህርት እስከማገድ የደረሰ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
 
921 ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሰራተኞች ላይ ደግሞ የተለያዩ ቅጣቶች መተላለፋቸውንም አስታውቀዋል።
 
ግጭቶቹን ለማስቆምም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ20 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን፣ ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል ፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.