Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል።
 
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
 
በዚህም በህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎችን ተመልክቷል።
 
የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ አቶ አበበ ጎዴቦ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት፥ የሽብር ድርጊት በሰው ህይወት፣ አካል እና ስነ ልቦና እንዲሁም ንብረትና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ አብራርተዋል።
 
ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የስራ ሃላፊዎች፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የፍትህ አካላት፣ ከህዝብ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዝርዝር ውይይት ማድረጉን አንስተዋል።
 
በዚህም ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን እና ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መገኘታቸውን አውስተዋል።
 
ረቂቅ አዋጁ መንግስት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ከሽብር ድርጊት እንዲጠብቅ፣ ጠንካራ የቅድመ መከላከልና ቁጥጥር ስራዎችን እንዲሰራና አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያሰጥ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በመዘርጋት እንዲተገብር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
 
የመንግስት አካላት የግለሰቦችን መብትና ነፃነት ከደፈሩ ተጠያቂነት የሚያስከትልባቸውና የሽብር ወንጀል ተጠቂዎች የሚካሱበትንና የሚቋቋሙበትን ስርዓት የሚፈጥር እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ህግ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ የምትገኝበት ቀጠና ለሽብር ድርጊት የተጋለጠ በመሆኑና ከውስጥም ከውጭም ስጋቶች በመኖራቸው መንግስት ወንጀሉን እንዲከላከልና እንዲቆጣጠር የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ቋሚ ኮሚቴዎቹ እንደሚፈልጉ በውሳኔ ሃሳባቸው አመልክተዋል።
 
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ መስተካከል ይገባቸዋል ያሏቸውን ሃሳቦች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
 
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
 
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ስብስባው የቀረቡለትን ስድስት ረቂቅ አዋጆች በመመርመር ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መርቷል።
 
የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣የሜርኩሪ ንጥረ ነገር ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው የሚናማታ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣
 
ዓይነ ስውራን ለንባብ የእይታ ችግር ላለባቸው እና በመደበኛ የንባብ ስልት ለማንበብ አካላዊ ችግር ላለባቸው ሰዎች የቀለም ጽሁፍ ህትመት ስራዎችን ተደራሽነት ለማመቻቸት የወጣው የማራካሽ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ከእነዚህ መካከል ናቸው።
 
እንዲሁም በኢትዮጵያና በኳታር መንግስት መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት እና ጥበቃ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ በአፍሪካ ህዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅና በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ የአፍሪካ ካምፓላ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አስተያያት ተሰጥቶባቸውና በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ተወስነው ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የተላኩ ረቂቅ አዋጆች ናቸው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.