Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ 50 ቢሊየን ብር የባንክ እዳ እንዳለበት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ 50 ቢሊየን ብር የባንክ እዳ እንዳለበት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የምክር ቤቱ አባል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና ካቢኔያቸው ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ኢንጅነር ታከለ ኡማ የከተማዋን ፀጥታ ለማስጠበቅ ህብረተሰቡን እና ወጣቶችን በማደራጀት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተማውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስም የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በቀጣይ ወር ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የሸገር የዳቦ ፍብሪካ እና ወደ ግንባታ የገባው የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

አያይዘውም ወደ ከተማዋ በ5 በሮች የሚገቡ የአርሶ አደር ምርቶችን ቀጥታ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበትን አሰራርን እየሰራን ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው።

ለከተማዋ ነዋሪ የዲጂታል መታወቂያ ለመስጠትም በከተማዋ ካሉት 116 ወረዳዎች ውስጥ 100 ወረዳዎች ላይ ስራቸው መጠናቀቁን እና ቀሪዎቹ ወረዳዎችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ተናግረዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ለ250 ሺህ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን፥ እስካሁን ለ150 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩንም ገልፀዋል።

ከቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላትም ከመኖሪያ ቤት ግንባታ መዘግየት፣ ከመሬት ወረራና ሰነድ አልባ ይዞታዎች ጋር ተያይዞ ለተነሱት ጥያቄዎች ምክትል ከንቲባው ምላሽ ሰጥተዋል።

ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ቅሬታዎች አስተዳደሩ በለውጥ ስራው ያለቁትን የማስተላለፍና የተጀመሩትንበፍጥነት የመጨረስ ስራ መሰራቱን ኢንጅነር ታከለ ገልጸዋል።

በከተማው በስምንት ወራት ብቻ ስምንት ሕንጻዎች ያሉት 1 ሺህ 700 ቤቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልፀዋል።

በቀጣይም በመሃል ከተማዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 38 ሺህ ቤቶችም ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ ብለዋል።

ኢንጂነር ታከለ የቤት ባለዕድለኞች ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ማቃለል እንደተቻለ ጠቁመው፤ አሁንም ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ቤቶች በፍጥነት ተገንብተው ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው የከተማ አስተዳደሩ 50 ቢሊየን ብር የባንክ እዳ እንዳለበትም ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገልጸዋል።

40/60 እና 20/80 የቤት ልማት መርሃ ግብር የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህ የሆነው ቤቱን የወሰዱ ሰዎች በትክክል ወለድና ኢንሹራንስ መክፈል ባለመጀመራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም 130 ሺህ ቤቶች ተገንብተው በወቅቱ ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው እንዲሁም በአጋጣሚ የተላለፉትንም ግለሰቦች ገብተው ኑሮ ባለመጀመራቸው እንደሆነም አብራርተዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የመንግስት ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ በመሆኑ ከባንክ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው።

ዘንድሮ በከተማው 500 ሺህ ቤቶች ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 175 ሺህ ቤቶች በመንግስት ቀሪዎቹ ደግሞ በባለሀብቶች የሚገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.