Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 786 ነጥብ 61 ቢሊየን ብር ሆኖ በቀረበው የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ መራ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 61 ቢሊየን ብር ሆኖ በቀረበለት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴው መራ።

ረቂቅ በጀቱ ዛሬ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፥ በረቂቅ በጀቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም አኳያ፣ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም፣ ቀጣይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን ማሳካት ማእከል በማድረግ እንዲሁም፥ የ2015-2019 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፉን መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ረቂቅ በጀቱን ተመልክቶ ውሳኔ ያሳለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጠቆሙ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ለ2015 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ ብር 347 ነጥብ 12 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218 ነጥብ 11 ቢሊየን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209 ነጥብ 38 ቢሊየን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 12 ቢሊየን የተያዘ ሲሆን፥ አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 61 ቢሊየን ብር ሆኖ ነው የቀረበው።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጅ ቁጥር 8/2014 ከተወያዩ በኋላ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ በመምራት ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.