Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሃገራት የተፈጠሩ የኢንቨስትመንት ትብብር ዕድሎችን በጥንቃቄ መጠቀም ይገባቸዋል – ም/ጠ/ ሚ አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሃገራት የተፈጠሩ ዓለምአቀፍ የኢንቨስትመንት ትብብር ዕድሎችን በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ሃያ የሚጠጉ አፍሪካ ሃገራት መንግሥታት የታደሙበት የብሪታኒያ -አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በለንደን ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያን እና የአፍሪካ ሃገራትን በመወከል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀመኮንን ንግግር አድርገዋል።

ለአፍሪካ አህጉራዊ ሽግግር ሃገራት የተፈጠሩ ዓለም አቀፋዊ የኢንቨስትመንት ትብብር ዕድሎችን በጥንቃቄ መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።

ከብሪታኒያ ጋር የተፈጠረው አህጉራዊ የኢቨስትመንት ትብብር ትልቅ አወንታዊ ማሳያ በመሆኑ የተፈጠረውን ዕድል ወደ ውጤት መቀየር ተገቢነቱን አንስተዋል።

በየደረጃው የተመዘገቡ ውጤቶች አፍሪካን ከከፋ ድህነት ለማላቀቅ እና ከውጭ ዕርዳታ ለመገላገል መሰረት እንደሚጥሉ ጠቁመዋል።

በአህጉር አቀፍ ደረጃ ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ ሽግግር የማረጋገጥ ስኬት፤ የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ በአብነት ልምድ መጋራት እንደሚቻል አስታውሰዋል።

የኢንቨስትመንት ትብብር የማጠናከር ተልዕኮ ፖለቲካዊ እርምጃ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ያለችውን የፖለቲካ፥ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራትን አብራርተዋል።

በመጨረሻም የጎደለውን በማረም፤ የተሻለውን በማስፋት ለላቀ አህጉራዊ ስኬት መረባረብ እንደሚገባ ማስመዝገባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በጉባኤው ላይ በአፍሪካ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚቀርቡ ሲሆን፥ ይህም በአህጉሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ስፋት እና ጥራት ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ታምኖበታል።

የኢንቨስትመንት ጉባኤው አፍሪካንና ብሪታኒያን በኢንቨስትመንት እና በንግድ በማስተሳሰር የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

መሰል ጉባኤዎች የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.