Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ የስራ ጉዟቸው ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ጋር ለንደን ላይ ተገኝተው ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳይ እና በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የሁለትዮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ተስፋ ሰጭ ቢሆንም በወንበዴው የህውሓት ቡድን ሴራ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሙት አስታውሰዋል።
የወንበዴው ህወሓት ቡድን ከነበረው ገደብ ያጣ የስልጣን ፍላጎት እና ከሁሉ በላይ እንደሆነ ዘመን የመሻገር የተንጠራራ ምኞት ሃገሪቱ እና ቀጠናውን ወደ ትርምስ ለመክተት ብዙ በደል መፈፀሙን አስረድተዋል።
በዚህ መሰረት መንግስት በትዕግስት እና በማስተዋል ያለፋቸውን ረጅም ጊዜ በንቀት በመተርጎም ፈፅሞ በሞራል እና በህግ የማይታለፉ ጥፋቶችን የወንበዴው ቡድን በድፍረት መፈፀም መቀጠሉን ተናግረዋል።
መንግሥትም ህግ የማስከበር እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን እና በትግራይ ክልል የተጀመረው ዘመቻ በፍጥነት እና በጥንቃቄ እየተመራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ታሪካዊ አጋር በመሆኗ፤ የሃገሪቱን ሰላም የሚፈትኑ የውስጥ ጉዳዮች እንደ ወዳጅ ሃገር እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።
መንግሥት በጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ንፁሃን ዜጎች ለችግሩ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ከለላ የሚሰጥበት መንገድ መመቻቸት እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ አካላት ነፃ እና አስተማማኝ መንገዶች እንዲያገኙ በመንግሥት በኩል የተጀመረው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን በመጠቆም እንቅስቃሴው እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
በቀጣይ ሃገራቱ በተለያዩ የትብብር ማዕቀፎች የጀመሩትን ጠንካራ ግንኙነት ትርጉምባለው ደረጃ ለማስቀጠል የጋራ መግባባት መፈጠሩን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.