Fana: At a Speed of Life!

ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ እንዲሆን ጥሪ ቀረበ –  የሃይማኖት መሪዎች

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ እንዲሆን የሃይማኖት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በመጭው እሁድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ለህዝበ ክርስቲያኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልእክታቸው የትንሳኤ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል።

በተለይ በየአካባቢው በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ወገኞችን በመመገብ፣ በማጠጣት እና በማልበስ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠር የሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ በመሆናቸው ሁላችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በዓሉን ሁሉም በደስታ እንዲያሳልፍ ለማድረግ የተፈናቀሉትን ማስብና መደገፍ አለብን ነው ያሉት።

የሀገሪቷን ሰላም ለማስጠበቅ ዘብ የቆሙ ኃይሎችም ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፣ “ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩና አስታዋሽ ያጡትን በማሰብና በመርዳት መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።

በአሉ ሲከበር እየተስፋፋ የመጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በጤና በባለሙያዎች የተላለፈውን ምክረ ሀሳብ በመተግበር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም ሰው ክፋትን ከልቡ በማስወገድ በክርስትና ህይወቱ ውስጥ ክርስቶስን መምሰል አለበት ብለዋል።

ከተበላሸ ህይወት በመጽዳት የፈጣሪን አብነት መከተልና የሰላም መሳሪያ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

በዓሉን በመተሳሰብና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአትዮጵያ ወንጌል አማኞች አባያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው።

ከፈጣሪ የተቀበልነውን ወንጌል ከቃል ባለፈ በመተግበር እርስ በርስ ተከባብሮ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባል ብለዋል።

”እኛ ታርቀን ሌሎችን ማስታረቅ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል” ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

መላው የወንጌል አማኞች ምዕመናን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጾምና ፀሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ህዝበ ከርስቲያኑ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችን በማሰብና ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘገባው የኢዜአ ነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.