Fana: At a Speed of Life!

ምዕመኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለኮቪድ-19 ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት – የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምዕመኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቫይረሱ የሚያዙና ወደ ጽኑ ህሙማን የሚያመሩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በዓላትን ተከትሎ በሚካሄዱ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች ሕዝቡ መዘናጋት በማሳየቱ ቫይረሱ በርካታ ሰዎችን በማጥቃት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ነው ያነሱት።
በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ኅብረተሰቡ ይህንን ቸልተኝነት መድገም የለበትም ያሉት ቀሲስ ታጋይ÷ በመሆኑም ሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ በርካቶች የሚታደሙበት በመሆኑ ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) በማንኛውም ሥፍራ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
ማስክ መግዛት ለማይችሉ የበዓሉ ታዳሚዎች አቅም ያለው ተጨማሪ ማስክ ይዞ እንዲመጣም ምክራቸውን ለግሰዋል።
ጎን ለጎንም የበዓሉ ታዳሚዎች የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር) በመያዝ እጅን በተደጋጋሚ በማጽዳት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ያም ብቻ ሳይሆን የቫይረሱ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሲባል ርቀትን ጠብቆ ሠላምታ መለዋወጥ እንደሚገባ ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል።
በዓሉ የሕዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና የሰላም እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ መከበር እንዳለበትና ለዚህም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የፍቅር በዓል እንዲሆን ቀሲስ ታጋይ በጉባኤው ስም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ130 ሺ 772 የደረሰ ሲሆን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 2 ሺህ 29 ደርሷል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.