Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ አዳነች የአረጋዊያን መርጃ ማእከል በመገኘት የበዓል ስጦታ አበረከቱ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው የአረጋዊያን መርጃ ማእከል በመገኘት የበዓል ስጦታ አበርክተዋል።

በጉብኝቱ ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ አረጋዊያኑ በከፈሉት ዋጋ ልክ እና ሀገር ለማቅናት በደከሙት መጠን የከተማ አስተዳደሩ ውለታቸውን በተገቢ መንገድና ሰዓት መመለስ ባለመቻሉ ይቅርታ ጠይቀዋል።

መከባበርን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትን እና ለሀገር በጋራ መቆምን የአሁኑ ትውልድ ከቀደምት አባቶቹ መማር ይገባዋል ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።

ለበዓል መዋያ እንዲሆንም 5 በግ፣ 2 በሬ፣ 86 ብርድልብስ፣ 50 ሊትር ዘይት፣ 200 ሳሙና፣ 150 ሳኒታይዘር፣ 200 ማስክ፣ 10 ኩንታል ጤፍ፣ 168 ጋቢ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የፍጆታ እቃዎችን ለአረጋዊያኑ አበርክተዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ የሚገኘው የአረጋዊያ መርጃ ማዕከሉ በ1962 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፥ ለ170 አረጋዊያን የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማምሻውን የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።

በጥራትና በፍጥነት እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ ለመስቀል ክብረ በዓል እንደሚደርስም በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

በጉብኝቱ ወቅት ከስራ ተቋራጩ እና ከባለሞያዎቹ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፥ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ ሙሉ ጊዜ ሰጥቶ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.