Fana: At a Speed of Life!

ም/ጠ/ሚ ደመቀ ህዝቡ ከመከላከያ ኃይል ጎን በመቆም ታሪካዊ ደጀንነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥሪ አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ህዝቡ ከመከላከያ ኃይል ጎን በመቆም ታሪካዊ ደጀንነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ትውልድ እና ሃገር በማዳን ተልዕኮ ላይ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪ አስተላለፉ፡፡
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ላለፉት ዓመታት በህውሃት ቡድን ቅጥ ያጣ ጥፋት እና ድፍረት “ትዕግስታችን” እንደፍርሃት እንዲሁም “አስተዋይነታችን” እንደድክመት እየተቆጠረ ህዝብና መንግስት ከልክ ያለፈ ዋጋ እንዲከፍሉ ማስገደዱ ይታወሳል ብለዋል፡፡
 
ከሁሉ በላይ በዚህ ኢትዮጵያ-ጠሉ ከሃዲ ቡድን ከቀናት በፊት የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ኃይል ላይ ጥቃት መፈጸሙንም አስታውሰዋል፡፡
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱ የአማራን ህዝብ ለመውረር በጠገዴ ቀራቀርና ሶሮቃ አካባቢ ያካሄደው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲሁም እስከጎንደር ለመዝለቅ ያሳየው ንቀት፣ እብሪት እና ድፍረት እጅግ አሳፋሪ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
 
ይሁንና የከሃዲውን ቡድን ረጅም ህልም በአጭሩ የቀጩት የመከላከያ ኃይል፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች ፈጣን የአጸፋ ምላሽ በመውሰድ ያስመዘገቡት ውጤት በእጅጉ የሚደነቅ እና የሚያስመሰግን ነው በማለት ነው ያስረዱት፡፡
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከሃዲ ቡድኑ ሴራ ለዘመናት ሰምና ወርቅ ሆኖ የኖረው የአማራ እና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት በዋዛ የሚበጠስ ሳይሆን፤ ታሪካዊ አንድነታቸው እና የተጋመደው ህብረታቸው እየጠበቀ ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋገር ይሆናል ብለዋል፡፡
 
ረጅም ጊዜ የቆየውን የሃገራችን መዋቅራዊ ችግር በማያዳግም አግባብ ለመፍታት ይህ ከሃዲ ቡድን መወገድ ይኖርበታል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
 
በተጨማሪም በተለያየ አቅጣጫ የቡድኑ መናጆዎችም በየአካባቢው ተጨማሪ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ በፍጥነት መነቀል ይኖርባቸዋል፡፡
 
አቶ ደመቀ የመከላከያ ኃይላችን የጀመረው ዘመቻ ፍጥነትና ጥንቃቄን በሚዛን አስቀምጦ የሚጓዝ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
 
ፍጥነቱ ከሃዲውን ቡድን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ ሲሆን፤ ጥንቃቄው ደግሞ ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ከጉዳት ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
 
በአሁን ጊዜ የመከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ግንባሮች ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ሲሆን፤ ደረጃ በደረጃ አኩሪ ገድል ማስመዝገብ መቀጠሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.