Fana: At a Speed of Life!

ሞዛምቢክ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆነች

አዲስ አበባ፣ሰኔ 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ሞዛምቢክ 192 የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን ድምፅ በማግኘት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆናለች፡፡

ከሞዛምቢክ በተጨማሪ ኢኳዶር፣ጃፓን፣ ማልታ እና ስዊዘርላንድ ትላንት በተደረገው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ምርጫ የአባልነት እውቅና የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ትላንት በተደረገው የፀጥታው ምክር ቤት የአባልነት ምርጫ ሞዛምቢክ 192፣ ኢኳዶር 190፣ ጃፓን 184፣ ማልታ 185 እና ስዊዘርላንድ 187 ድምፅ በማግኘት ነው አባል መሆን የቻሉት፡፡

የሞዛምቢኩ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ በሰጡት አስተያየት፥ ሀገራቸው ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ጥረት ለሚያደርጉ የአፍሪካ ሀገራት በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምጽ ትሆናለች ብለዋል።

“ይህ ለሀገራችን ታሪካዊና ሀገራችን ልትኮራ የምትችልበት ወቅት ነው” ብለዋል ፕሬዚደንቱ፡፡

ሞዛምቢክ የግጭትን የማስወገድ እርምጃዎችን የማበረታታት ልምድ አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ከሁሉም በላይ የሰላም ድርድር መፍትሄዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ሞዛምቢክ የማይናወጥ አቋም እንዳላት የቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ ያመላክታል።

15 አባላት ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ፣ ሩሲያ እና ቻይናን በቋሚ አባልነት ያቀፈ ሲሆን፥ ሌሎች ቋሚ ያልሆኑ 10 መቀመጫዎች እንዳሉት ይታወቃል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.