Fana: At a Speed of Life!

ሠሞኑን በመተከል ዞን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሠሞኑ በመተከል ዞን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ አንጻራዊ ሠላም በመመለስ ላይ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡

የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ÷ጸረ-ሠላም ኃይሎች በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እና በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት ማፉን ገልጸዋል፡፡

ሃላፊው የክልሉ መንግስት በድርጊቱ ጥልቅ ኃዘን እንደተሰማው በመግለጽ÷ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሠቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ሀላፊው አያይዘውም ጥቃት አድራሾቹ ቀደም ሲል በወምበራ ወረዳ ኮንግ ማዕከል የብልጽግና ፓርቲ እና የመንግስት ደጋፊ ናችሁ በሚል በህብረተሰቡ ላይ የግድያ፣ የማገት እና የማፈናቀል ድርጊቶችን መፈጸማቸውን አስታውሰዋል፡፡

በሃምሌ ወር በጉባ ወረዳ ያቡሉ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ መሠል ጥቃት አድርሰዋል ያሉት አቶ አበራ ÷በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ የጸጥታ ኃይል በተወሰደባቸው እርምጃ አብዛኞቹ ከመደምሰሳቸውም ባለፈ 168 አባላቶቻቸውና ግብረ-አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ከሳምንት በፊት ደግሞ በወምበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ ገብተው 36 የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የቀበሌ አመራሮችንና ሚሊሻዎችን፣ እንዲሁም ታዋቂ ሰዎችን አግተው ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ እና ከብቶችን እንዲሰጧቸው ሲያስገድዱ እንደነበርም ነው አቶ አበራ የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት በቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ ገብተው ባደረሡት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ኤጳር ቀበሌ ማዕከልን ጨምሮ በዞኑ የጸጥታ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ችግሩ በተፈጠረ ማግስት ወደ ቦታው መድረሳቸውን የገለጹት አቶ አበራ ÷ ጸጥታውን የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ለማረጋጋትና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው እየሰሩ መሆኑን በመጠቆም የሠላም ውይይቶች በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

በስጋት ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ማዕከሉ እየተመለሱ ስለመሆናቸውም ነው አቶ አበራ ጨምረው የገለጹት፡፡

ከዚያም ባለፈ የቤኒሻንጉል እና የአማራ ክልል መንግስታት ለሁለቱ ክልል ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዲሁም በቀጠናው ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ከዚህ ቀደም የጀመሯቸውን ተግባራት የበለጠ በማጠናከር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

እየተሠሩ ካሉት የማረጋጋት ሥራዎች ጎን ለጎን በስጋት ምክንያት ከቤታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊ የሰብዓዊ ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የተፈጸመውን ጥቃት በ2 ብሔሮች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ እየተገለጸ ያለው መረጃ ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸው ÷ ጸረ-ሠላም ኃይሎቹ ጥቃት ያደረሱት “ከእኛ ሀሳብ በተቃራኒ ቆማችኋል” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እንጂ ብሔርን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እየተገለጸ ያለው አሃዝ መሠረተ ቢስ ነው ያሉት አቶ አበራ÷ የሟቾችን ቁጥርም ሆነ የደረሰው የጉዳት መጠን ትክክለኛ መረጃ በመጣራት ላይ ሲሆን በቅርቡ ለህብረተሰቡ ይገለጻልም ነው ያሉት ፡፡

ከዚያም ባለፈ”አንዳንዴ ሞተዋል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠፍተዋል” ሲባሉ የነበሩ 27 ሰዎች ተገኝተው ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀላቸውንም ኃላፊው አንስተዋል፡፡

በክልሉ በተለይም ለውጡን ተከትሎ ከመጣው የፖለቲካ ስነ-ምህዳር መስፋት ጋር ተያይዞ ጥምረት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት ቦዴፓ፣ ቤህኔን ሰዴድ እና ጉህዴን የፖሊቲካ ድርጅቶች ህግን አክብረው ከመንቀሳቀስ ይልቅ እየተጓዙበት ያለው ህገ-ወጥ አካሄድ ህብረተሰቡን ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ጉህዴን ወጣቶችን የድርጅቱ ወታደሮች ትሆናላችሁ በሚል ግልጽ ቅስቀሳ ሲያደርግና መልምሎ ሲያሰለጥን እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

ሠላም ወዳዱ ሕዝብ እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች የያዙት እኩይ ዓላማ እንዲመክን ከማድረግ ባሻገር፣ የክልሉ መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር እየሠራ ላለው ህግ የማስከበር ሥራ የተለመደ ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ አበራ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.