Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ሸቀጦችን ወደ አፍሪካ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው – ሰርጌ ላቭሮቭ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ሩሲያ የምግብ ምርቶችን ወደ አፍሪካ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ሲሉ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ፡፡

ምንም እንኳን ሩሲያ በምዕራባውያን ማዕቀብ ጫና ውስጥ ብትሆንም ለአፍሪካውያን ቃል የገባችውን የምግብ፣ የማዳበሪያ፣ ኃይል እና ሌሎች ሸቀጦችን ታቀርባለች ብለዋል፡፡

“ሞስኮ አፍሪካውያንን ልታስርብ ነው የሚለው የዩክሬን እና ምዕራባውያን ፕሮፖጋንዳ መሰረተ ቢስ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በዓለም ዙሪያ ተደራሽ የምታደርጋቸው የምግብ ምርቶች አስፈላጊ መሆናቸውን እንደምትገንዘብ እና በተለይም የምግብ አቅርቦቶቹ ማህበራዊ ኑሮን በማረጋጋት ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዩክሬን ሞስኮ በጥቁር ባሕር የሚገኘውን ወደብ በመዝጋት ለገበያ ሊሰራጭ የነበረን ከ20 ሚሊየን ቶን በላይ የምግብ ሸቀጥ እንዳይንቀሳቀስ አድርጋለች በሚል ትወቅሳለች።

ሩሲያ በአንጻሩ ውንጀላውን በማስተባበል በወደቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይኖር ዘንድ እየሰራች መሆኗን ትገልጻለች።

ሩሲያ በማንኛውም ሀገር ላይ ጫና አትፈጥርም ያሉት ላቭሮቭ በተለይም የአፍሪካ መንግስታት የሉዓላዊነት እና የእድገታቸውን መንገድ ራሳቸው እንዲወስኑ መብታቸውን ታከብራለች ብለዋል፡፡

ሞስኮ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈቱ የተቀመጠውን  መርህ እንደምታከብር መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.