Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በዩክሬን ግጭት ጣልቃ በሚገባ ሀገር ላይ መብረቃዊ ጥቃት እንደምትፈፅም ፕሬዚዳንት ፑቲን አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ20፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን በዩክሬን ግጭት ጣልቃ በሚገባ ሀገር ላይ ሀገራቸው መብረቃዊ ጥቃት በመፈፀም አፀፋውን እንደምትመልስ አስጠነቀቁ።

ፕሬዚዳንቱ ከሀገሪቱ የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር በሞስኮ ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት፥ የውጭ ሀይሎች በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ከሆነ ሀገራቸው “ማንም ሀገር ያልታጠቃቸው” ያሏቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች በመጠቀም መብረቃዊ ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

“የውጭ ሀይሎች እየተካሄደ ባለው ጦርነት ጣልቃ ከገቡ እና ስጋት ከደቀኑብን ፈጣን ምላሽ እንደምንሰጥ ሊያውቁ ይገባል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

የሩሲያ ባለሥልጣናትም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ፑቲን ጠቁመዋል፡፡

ሞስኮ በዩከሬን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች አንስቶ ምዕራባውያን ሀገራት ፀረ-ታንክ እና ፀረ-አውሮፕላን መሳሪያዎችን የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን ለኪዬቭ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ቆተዋል፡፡

ሞስኮ በበኩሏ ለዩክሬን የሚደረጉ የጦር መሳሪያ ድጋፎች ግጭቱን የበለጠ የሚያባብሱ እና የሰላም ተስፋዎችን የሚያጨልሙ ናቸው በማለት ይህንን ጣልቃ ገብነት ስትኮንን ቆይታለች፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌይ ላቭሮቭ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ እንደተናገሩትም፥ ኔቶ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ በማቅረብ በእጅ አዙር ከሩሲያ ጋር ጦርነት ገጥሟል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሞስኮ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን RS-28 ሳራማት አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ የሞከረች ሲሆን፥ ሚሳኤሉን የታጠቀ ወታደራዊ ክፍል ልታሰማራ መሆኑንም አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ እና የኔቶ አባል ሀገራት በአንፃሩ ምንም አይነት የሀይፐርሶኒክ ሚሳኤልን እንዳልታጠቁ አር ቲ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.