Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ግጭት ውስጥ በገባችባቸው የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ ከነዳጅ ሽያጭ 98 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በተጀመረ በ100 ቀናት ውስጥ ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልከው ነዳጅ 98 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች ተብሏል፡፡

ምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያን ለማግለል እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በርካታ የኢኮኖሚ ማእቀቦች በመጣል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቷን ለማቋረጥ ቢሞክሩም፥ ሞስኮ ከነዳጅ ሽያጭ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘት መቀጠሏን መቀመጫውን ፊንላንድ ያደረገ የሃይል እና ንጹህ አየር ምርምር ማእከል ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡

የምርምር ማዕከሉ ይህንን ሪፖርት ያወጣው ኪዬቭ የሩሲያን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ ምዕራባውያን ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲያቋርጡ መጠየቋን ተከትሎ ነው፡፡

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አብዛኛውን የነዳጅ ምርት ከሩሲያ የሚያስገባው የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ላይ እገዳ ለመጣል መስማማቱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን ህብረቱ በዚህ አመት ከሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚገባውን የጋዝ ምርት በ2/3 ለመቀነስ ቢያቅድም እገዳው የታለመለትን ግብ ሊመታ አልቻለም ነው የተባለው፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነሩሲያ ከዩክሬን ጋር ግጭት ውስጥ በገባችባቸው የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት 61 በመቶውን የሩሲያ ነዳጅ ገዝቷል፡፡

ይህም በገንዘብ ሲተመን 60 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ከሩሲያ ነዳጅ ከሚያስገቡ ሀገራት ውስጥ ቻይና በ13 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በመግዛት ቀዳሚውን ድርሻ ስትይዝ፣ ጀርመን 12 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ጣሊያን 8 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የነዳጅ ግዢ ፈጽመዋል መባሉን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.