Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የምዕራባውያንን ማዕቀብ እንድትቋቋም ህንድ እያገዘቻት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ምዕራባውያን የሚጥሉባትን ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ እንድትቋቋም ህንድ እገዛ እያደረገችላት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሞስኮ ቀደም ሲል ህንድ የሩሲያን ነዳጅ ዘይት በዶላር ወይም በዩሮ እንድትገዛ እቅድ ያቀረበች ሲሆን÷ሌሎች እቃዎችን ደግሞ በሩሲያ የመገበያያ ገንዘብ ሩብል ክፍያዎችን እንድትፈፅም አዲስ እቅድ ማውጣቷ ተመላክቷል፡፡
 
በአዲሱ የግብይት ውሳኔ ሃሳቦች ላይ የፋይናንስ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በተገኙበት በሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ እና በህንድ አቻዎቻቸው መካከል ውይይት ተደርጓል ነው የተባለው፡፡
 
ብሉምበርግ እንዳስነበበው አዲሱ ስርዓት ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት የሚያጋጥማትን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም በሀገር ውስት ምንዛሬዎቿ ላይ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ የታሰበ ነው፡፡
 
ቀደም ሲል የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሪንዳም ባግቺ ÷ህንድ ከሩሲያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የኢንተር ሚኒስትሮች ቡድን ከሞስኮ ጋር የመክፈያ ዘዴዎችን በተመለከተ መፍትሄዎችን እያፈላለጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ምዕራባውያን ህንድ ከሩሲያ ጋር ያላትን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንድታቆም ጫና ቢያደርጉባትም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ በኋላ ህንድ የንግድ ትስስሯን በማጠናከር የሩሲያ የኢኮኖሚ አጋር ሆና ቆይታለች፡፡
 
በፈረንጆቹ 2021/22 የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት ውስጥ ህንድ ከሩሲያ የምታስገባው የገቢ ምርት ወደ 8 ነጥብ 69 ቢሊየን ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን÷ ይህም በ2020/21 ከተመዘገበው የገቢ ምርት መጠን የ 5 ነጥብ 48 ቢሊየን ዶላር ብልጫ ማሳየቱን የሕንድ መንግሥት አስታውቋል፡፡
 
በተመሳሳይ ህንድ ለሩሲያ የምትልከው የወጪ ምርት በፈረንጆቹ 2020/21 ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን÷ በአውሮፓያኑ 2021/22 ወደ 3 ነጥብ 1 88 ቢሊየን ዶላር ማደጉን አር ቲ ዘግቧል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.