Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የቀጠናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ሩሲያ የቀጠናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡

የሩሲያ አምባሳደር ያቭጋኒ ተርክን ኢትዮጵያ የራሷን እና የቀጠናውን ደህንነት ለመጠበቅ በምታደረገው ጥረት የሩሲያ መንግስት ድጋፍ እንደማይለያት ገልጸው፤ አገራቸው የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ያቭጋኒ ተርክን መንግስታቸው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ደህንነትን ለማጠናከር በተለያየ መንገድ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀጠናውን ደህንነት በተሻለ መልኩ ማጠናከር የሚቻለው ፖሊቲካዊ መፍትሄዎችን በማጠናከር እንደሆነ ያመለከቱት አምባሳደሩ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያና ሩስያ ለበርካታ ዓመታት በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል ።

በተለይ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በነበረችበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራታቸውን ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ደህንነት እና ፀጥታ በዋናነት ማስጠበቅ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን መቀበል አለብን ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህም ሩሲያ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል ለማጠናከር ሰፊ እርዳታዎችን ሰጥታለች ብለዋል ።

ማንኛውም ሀገር የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ከሁሉም ቅድሚያ የኢኮኖሚ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት የጠቆሙ ሲሆን፤ በዚህም የሀገራችው መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ሩሲያ የቀጠናውን ደህንነት ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ሁለንተናዊ መልክ እንዳለውም አመልክተዋል።

በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ እያደረጉት ያለው ጥረት የሶስቱ ሃገራት ጉዳይ ቢሆንም፤ የሀገራቱን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍ አስታውቀዋል ።

“ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ግዙፍ ሀገር ናት፤ የቀጠናው ሀገራት የደህንነት ጉዳዮች የሚወስኑት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው”ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና ደህንነት የሚሰፍን ከሆነ የቀጠናው ሰላም እና ደህንነትም የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ሀገራቸው የኔውክሌር ሃይልን ለሰላማዊ ተግባር ለማዋል ከኢትዮጵያ ጋር በጋራእንደምትሰራ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ተጠቃሚ ሃገሮች አባል ከሆነች እኛ ለመርዳት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እኤአ 2019 በሩሲያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደው በአፍሪካ-ሩሲያ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት በኒውክሌር መስክ መሰረታዊ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

የሁለቱ ሃገራት ወቅታዊ የኔውክሌየር የትብብር ስምምነት በዚህ ዓመት ታህሳስ ላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ የኒውክሌር ሃይልን ለልማት መጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት ካፀደቀ በኋላ ተግባራዊ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘርፉ ተጨማሪ አዳዲስ የመግባቢያ ሰነዶችን ለመፈራረም መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ስምምነቶቹ የኒውክሌር ሃይል አጠቃቀም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚረዱ በአቅም ግንባታ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኒውክሌር ትብብር በሃይል ማመንጫ ብቻ የሚወሰን እና በአጋጣሚ የሚደረግ አለመሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ ፣ የኒውክሌየር የሀይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ውስብስብ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፤ ጊዜ፣ ጥረትና ገንዘብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

የተለመደው የኒውክሌር ጣቢያ ግንባታ የጊዜ ገደብ ወደ አስር ዓመት የሚጠጋ ሲሆን፤ ግንባታው እስኪከናወን ሌሎች ተያያዥ እቅዶችን ወደ ተግባር በመለወጥ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ብለዋል።

የሃይል ማመንጫ ጣቢያው ከመጠናቀቁ በፊት በሕክምና ዘርፍ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ቢተገበር ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

“በተጨማሪ በየዓመቱ ከሚሰበሰበው የሰብል ምርት 25ከመቶ በበሽታዎች እና በተለያዩ ምክንያቶች ይባክናል፤ ይህንን ለመቀነስና በሌሎችም ኢንዱስትሪዎች ላይ የኒውክሌር ሀይል ልማት ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነም መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ የቴክኖሎጂ ትብብሮች በሌሎችን የቴክኖሎጂዎች በማበልጸግ ዘርፎችም በጋራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.