Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የኮቪድ-19 ክትባትን በ2 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ማምረት እንደትምጀር አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሩሲያ አዲስ ያገኘችውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል ልትጀምር መሆኑን አስታውቃለች።
 
የመጀመሪያው ዙር የክትባቱ ምርትም በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚጀምርም የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
 
በመጀመሪያው ዙር የሚመረተው ክትባት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል መሆኑን ያስታወቁት የጤና ሚኒስትሩ ሚክሃይል ሙራሽኮ፥ ክትባቱ መጀመሪያ የሚሰጠውም ለህክምና ባለሙያዎች እንደሆነም አስታውቀዋል።
 
የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቱ ለህክምና ባለሙያዎች ተሰጥቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለህዝቡ መሰጠት እንደሚጀምርም ነው ሚኒስተሩ ያብራሩት።
 
ሩሲያ የመጀመሪያ ዙር የክትባት ምርትን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል ብትልም፤ የሀገሪቱ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈንድ ተቋም ግን ክትባቱ በስፋት ተመርቶ ለዓለም በሚሰራጭበት ሁኔታ ላይ ድርድር እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
 
ስለ ክትባቱ ደህንነት እና አስተማማኝነት ላይ ለተነሳው ጥያቄም የጋምልያ የጥናት ማዕከል ኃላፊ አሌክሳንደር ጊንስበርግ፥ ክትባቱ ሁሉንም ሳይንሳዊ ሂደቶችን አልፎ የተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
በክትባቱ ላይም የሙከራ ሂደቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች እና እንስሳት ላይ በቂ ክትትል መደረጉንና ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ሁሉም በቫይረሱ እንዳልተያዙ መረጋገጡንም አስታውቀዋል።
 
የጋምልያ የጥናት ማዕከል ኃላፊው አክለውም፥ አዲሱ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ለህፃናትም ይሁን እድሜያቸው ለገፉ ሰዎችም የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአወሳሰድ መጠን ላይ ሊለያይ ስለሚችል ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደበት መሆኑን አስታውቅዋል።
 
ሩሲያ ባሳለፍነው ማክሰኞ ነበር “ስፑትኒክ ቪ” በሚል የሰየመችውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባይ ይፋ ያደረገችው።
 
የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኑን በእለቱ ማስታወቃቸውም ይታወሳል።
 
ሆኖም ግን የዓለም ጤና ድርጅት በክትባቱ ዙሪያ ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም በትናንትናው እለት ማስታወቁ አይዘነጋም።
 
የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱን የሩሲያ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ለመመዘንም ከሀገሪቱ በቂ መረጃ እንዳላገኘም ነው በመነገር ላይ የሚገኘው።
 
ምንጭ፦ Aljazeera እና aa.com
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.