Fana: At a Speed of Life!

ራማፎሳ ሃገራት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን እንዲተገብሩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ የአፍሪካ ሃገራት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን እንዲተገብሩ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሃገራቱ ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለሚሆነው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህንን ያሉት ትናንት በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት አጋማሽ ዓመት ስብሰባ ላይ ነው ተብሏል፡፡

በስብሰባው ላይ የአህጉሪቷ የ2063 አጀንዳ የተነሳ ሲሆን አጀንዳውን ለማሳካት በተሰራው ስራ ደስተኛ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦችን ማጠናከር ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና መሰረት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለነጻ ንግድ ቀጠናው ላሳዩት ተግባርም አመስግነዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ልማት ማህበረሰብ፣ የምስራቅ አፍሪከ ሃገራት እና የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ማህበር መሳተፋቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ስምንት ጥቅል እና ሰባት ዝርዝር ዓላማዎች አሉት።

እስካሁን 54 አባል ሃገራት የፈረሙበት ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ዓላማ በአባል ሃገራት መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ላይ ግብርን በማስቀረት እርስ በእርሳቸው የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ይነገራል።

ከጥቅል ዓላማዎቹ ውስጥ በአፍሪካ የተቀናጀ ጥቅል የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ለመፍጠር የዕቃ፣ የአገልግሎትና የሰዎች ዝውውርን መፍጠር እንዲሁም በስምምነት ላይ የተመሰረተ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ነጻ ገበያን መፍጠር ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን 2011 ዓ.ም መጋቢት 12 ቀን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቋ የሚታወስ ነው፡፡

 

 

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.