Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትአስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ፣ እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሠላም አደረሳችሁ!
 
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ተስፋ፣ ፍቅርና ወንድማማችነትን ያስተምረናል፡፡ በርሱ ልደት ምክንያት በተለያዩ ችግርና መከራ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ተስፋና ክብር አገኙ፡፡ የተወለደው ህጻን ሐብታሞችንና ድሆችን፣ ነገሥታትንና እረኞችን እኩል ደስ አሰኛቸው፡፡ ይህም የሰው ልጅ ምንም ያህል በመካራ ቢፈተን የተስፋና ተድላ ዘመን ማየቱ አይቀሬ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ከዚህ አንፃር አገራችን ባሳለፍናቸው ዓመታት በብዙ መከራና ሥቃይ ውስጥ አልፋለች፡፡
 
አሸባሪዎቹ ትህነግና ሸኔ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ሕይወት አጨልመዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሐብትና ንብረት አውድመዋል፡፡ በኢየሱስ ዘመን ንጉሥ ሄሮደስ ህጻናትን አስገድሎ እናቶችን ለልብ ስብራት እንደዳረገ ሁሉ፣ ዛሬ አሸባራቹ ሸኔ እና ህወሓት ብዙ ህጻናትና እናቶቻችንን ለመከራ ዳርገው አሰቃይቷቸዋል፡፡
 
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ አንድ የማይናወጥን እውነት ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ይህም የትኛውም በክፋት የተሞላ ሐሳብና ድርጊት በመጨረሻ መሸነፉ አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡ በ ህወሓትና ሸኔ ህዝባችን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የጥፋት ድርጊት በህዝባችን የአንድነት መንፈስ እና የእግዛብሔር እርዳታ እየተሸነፈ ነው፡፡ ይህም በዜጎቻችንና አጋሮቻችን ዘንድ ታላቅ ተስፋ ፈጥሯል፡፡
 
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ፍቅርን አስተምሮናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው ሥጋ ለብሶ በከብቶች በረት ተወለደ፡፡ የክብር ዘውድ ትቶ ከሰው ጋረ መኖር ፈለገ፡፡ በዚህም ለሰው ልጅና ለዓለም ያለውን ፍቅር ገለጸ፡፡ እኛም ደግሞ እንድንዋደድና ፍጥረታትን ሁሉ እንድንወድ፤ መልካምነትና ፍትሐዊነት እሴታችን እንዲሆን፤ እየሱስ ለሁሉም ፍጥረታት የደስታ ምንጭ እንደሆነ ሁሉ ሀብታም ድሓ ሳንል ለህዝባችን ስንል ዝቅ ብለን በማገልገል የህዝባችን የደስታ ምንጭ እንሆን ዘንድ ትምህረት ልንወስድበት ይገባል፡፡
 
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ወንድማማችነታችንን ያስታውሰናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አባታችን ሆይ›› በማለት እግዚአብሔርን ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር የሁላችን ‹‹አባት›› ከሆነ፣ ሁላችንም ‹‹ወንድማማቾች›› መሆናችንን ያሳየናል፡፡ በአገራችን የሚታዩት የቋንቋ፣ የብሔርና ሌሎች ብዘሃነት ሊለያዩን የሚገቡ ጉዳዮች አይደሉም፣ ይልቁንም በወንድማማችነት መንፈስ ይበልጥ አንድ ላይ ሊያሰባስቡን እንደሚገባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምረናል፡፡ እኛም የኢትዮጲያ ልጆች ብዝሃነታችንን የውበታችንና የአንድነታችን መሰረት አድረገን በማየት በይበልጥ መከባበርና መዋደድ ይኖርብናል፡፡
 
በነገ ዕለት የምናከብር የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል፣ ድህነት፣ ጥላቻ መለያየትን ለማሸነፍ ተስፋ እንድንሰንቅ፣ ለአገርና ለህዝባችን ያለንን ፍቅር በአገልጋይነት መንፈስና በትህትና እንድናሳይ፣ የብሔርና የቋንቋ ብዝሃነታችን ውበታችን መሆኑን ተገንዝበን በወንድማማችነት ማዕቀፍ ወደፊት ለመራመድ እንደሚያነሳሳን ተስፋ አለኝ፡፡ በተለይም ደግሞ እየሱስ ክርስቶስ የወደቁትን በማንሳት፤ ለታመሙት ፈውስ በመስጠት ለሰው ልጅ ሁሉ መድሃኒት እንደሆነው ሁሉ፤ እኛም በዓሉን ስናከበር፤ በጦርነቱ ምክንያት ከሞቀው ቄሄያቸውና ንብረታቸው ተፈናቅለው መንገድ ዳር ለወደቁ፤ ለታረዙና ተጎድተው በህመም ለሚሰቃዩ ወገኖቻችን የለንን በማካፈል አብረውን እንዲደሰቱ፤ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እና ወደመደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ የገባናል፡፡
 
በድጋሚ እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሠላም አደረሳችሁ!
 
ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር
ታህሳስ 28፣ 2014 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.